በዞኑ ከ18ሺህ በሚበልጥ ሄክታር መሬት ላይ ተከስቶ የነበረው ተምች ማስወገድ ተቻለ

54
ሽሬእንዳስላሴ ነሀሴ 8/2010 በትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን 18ሺህ 845 ሄክታር በሚሸፍን መሬት ላይ ተከስቶ የነበረው የአሜሪካ መጤ ተምች ማስወገድ መቻሉ ተገለጸ፡፡ በዞኑ አስተዳደር ጽህፈት ቤት የስነ አዝርዕት ባለሙያ አቶ አዱኛ ገብረ ለኢዜአ እንደተናገሩት ተምቹን ማስወገድ የተቻለው መንግስት ባመቻቸው መደኃኒት ታግዞ የግብርና ባለሙያዎች በሰጡት ድጋፍና አርሶ አደሮችም ባህላዊ ዘዴን በመጠቀም ባደረጉት የተቀናጀ ጥረት ነው፡፡ በዚህ ስራ ከአራት ሺህ  በላይ አርሶ አደሮች ከመሳተፋቸው  በላይ ዘጠና አራት ሊትር ኬሚካል ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ አቶ አዱኛ እንዳሉት ከተምቹ ነጻ የሆነውን አዝርእት ተመልሶ  ሊጠቃ ስለሚችል አርሶ አደሩ ማሳውን ደጋግሞ እንዲፈትሽ፣  ባለሙያዎችም የቅርብ ክትትልና ድጋፋቸውን መቀጠል አለባቸው፡፡ መጤ ተምቹ በአብዛኛው በቆሎን የሚያጠቃ በመሆኑ አርሶ አደሮች ልዩ ትኩረት ማድረግ እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡ በዞኑ ታህታይ ቆራሮ ወረዳ የበለስ የገጠር ቀበሌ አርሶ አደር መብረሃቶም ተክሉ በሰጡት አስተያየት በግማሽ ሄክታር ተከስቶ የነበረው የአሜሪካን ተምች በመደኃኒት ርጭት መከላከል እንደቻሉ ተናግረዋል፡፡ በመከላከሉ ስራ ላይ  የአካባቢው አርሶ አደሮች በመሳተፍ ድጋፍ እንዳደረጉላቸውም ጠቅሰዋል፡፡ የዚሁ ቀበሌ  አርሶ አደር ነጨይ ተስፋዬ በበኩላቸው አንድ ሄክታር ማሳቸው በተምቹ ተወሮ የከፋ ጉዳት ሳይደርስ በባህላዊ መንገድና  በመደኃኒት ርጭት ታግዘው መከላከላቸውን ገልጸዋል፡፡ በትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን በተያዘው የመኸር ወቅት  በተለያዩ ሰብል  ከተሸፈነው 224 ሺህ 200 ሄክታር መሬት ከሰባት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል፡፡          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም