በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በደረሰ የትራፊክ አደጋ የ16 ሰዎች ህይወት አለፈ

61
ደብረ ብርሃን ነሀሴ 8/2010 በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን አንጎለላና ጠራ ወረዳ በደረሰ የተሽከርካሪ አደጋ የ16 ሰዎች ህይወት ማለፉን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ። በመምሪያው የመረጃ ትንተና ባለሙያ ኢንስፔክተር አድማሱ ኃይለስላሴ እንደገለጹት አደጋው የደረሰው ከአዲስ አበባ ወደ ደብረ ብርሃን ሲጓዝ የነበረ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3፣ 03389 ኦሮ የሆነ የህዝብ ማመላለሻ አይሱዙ ከደብረ ብርሃን ወደ አዲስ አበባ ከሚጓዝ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3፣ 55830 ኢት ከሆነ ሲኖትራክ ጋር በመጋጨቱ ነው፡፡ በወረዳው ጨፋና ቀበሌ ልዩ ስሙ ጽጌሬዳ በተባለ ስፍራ ላይ ዛሬ ከቀኑ 6፡00 ሰዓት አካባቢ በደረሰው በዚህ አደጋ ሁለቱን አሽከርካሪዎች ጨምሮ የ12 ሰዎች ህይወት ወዲያውኑ ሲያልፍ አራት ሰዎች ደግሞ ሆስፒታል ከደረሱ በኋላ መሞታቸውን ተናግረዋል። ከባድና ቀላል የመቁሰል አደጋ የደረሰባቸው 16 ሰዎችም በደብረብርሃን ሪፈራል ሆስፒታል እርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑን ኢንስፔክተር አድማሱ ተናግረዋል። የአደጋው መንስኤ እየተጣራ መሆኑን ገልጸው ህይወታቸውን ያጡ ግለሰቦች አስክሬንም ወደ አዲስ አበባ ዳግማዊ ምኒሊክ ሆስፒታል ለምርመራ መላኩን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም