አዲሱ ዓመት የኢትዮጵያን ሰላምና አንድነት የበለጠ በማጠናከር የምንሻገርበት ይሆናል

67

መስከረም 02 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ፈተናዎች በገጠሟት ቁጥር እንደ ብረት የምትጠነክር አገር በመሆኗ "አዲሱ ዓመትም ሰላምና አንድነቷን የበለጠ የምታጠናክረበት ይሆናል" ሲሉ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ወርቅነሽ ብሩ ተናገሩ።

የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ወርቅነሽ ብሩ ከኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ አባቶች ጋር የታላቁ ሕዳሴ ግድብን ግንባታ ሂደት ተመልክተዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ኢትዮጵያ የቀደምት የአባቶች ታሪክን ለመድገምና አዲስ ታሪክ ለመስራት እያካሄደች ካለው እንቅስቃሴ አንዱ ማሳያ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ነው።

"ሰላም ሚኒስቴር ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ሰላም እንዲኖራቸው ምኞቱና ስራው ነው" ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ በወቅቱ ኢትዮጵያ ውስጣዊና ውጫዊ ፈተናዎች እንደገጠሟት ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን ለማፍረስና ሉዓላዊነቷን ለመዳፈር ሁሌም ውስጣዊ ሃይሎችና ከጀርባ ሆነው ድጋፍ የሚሰጡ ውጫዊ ጠላቶች ሲዘምቱባት መቆየታቸውን አስታውሰው፤ ኢትዮጵያዊያን ችግሮቹን በድል ለመወጣት በአንድነት በመቆም ታላቅ ታሪክ ሲያስመዘግቡ መኖራቸውን አስታውሰዋል።

ዛሬም 'ሕዳሴ ግድብ አይሞላም' የሚሉ የውጭ ሃይሎች ምኞትን ከንቱ በማስቀረት "ኢትዮጵያ በራሴ ህዝብ ሃይልና አቅም አለኝ" በማለት ሁለተኛውን የግድቡን ውሃ ሙሌት ሂደት በማጠናቀቅ በድል ማለፏን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የሉዓላዊነቷን ጉዳይ በቀይ መስመር አስምራ እየተሻገረች መሆኑን ገልጸው፤ "በአዲሱ ዓመትም ያጋጠሙንን ፈተናዎች ተወጥተን ወደ ልማትና ወደ ሰላም እንድትሻገር ያደርጋል" ብለዋል።

በየዘመኑ ኢትዮጵያን የሚያፈርስ ጠላት ሲመጣ ኢትዮጵያዊያንን አንድ እንደሚያደርግ አውስተው፤ ኢትዮጵያን እንደ ብረት የሚያጠናከር በመሆኑ "አዲሱ ዓመትም ሰላምና አንድነትን የሚያመጣ ነው" ብለዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ የገጠማትን ችግር እንደ ዕድል በመጠቀም ወደ ተሻለ ደረጃ ለመሻገር መተባበር እንደሚገባ አብራርተዋል።

በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ የሚሳተፉ ኢትዮጵያን ወደ ልማት ለማሻገር ትልቅ ስራ እየሰሩ መሆኑን ጠቁመው፤ የግንባታውን ደረጃ በማየታቸው ከሚሰማው የበለጠ የሚያኮራ ስራ መሆኑን ገልጸዋል።

በአዲሱ ዓመት ዋዜማ በግድቡ ግንባታ ስፍራ ተገኝተው ጸሎትና ቡራኬ ያደረሱ የሃይማኖት አባቶችንም አመስግነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም