የጉሙዝ ማህበረሰብ ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ ለአካባቢው ሰላም መረጋገጥ የድርሻውን እንዲወጣ ተጠየቀ

168

አሶሳ፣ መስከረም 01 ቀን 2014 (ኢዜአ) የጉሙዝ ማህበረሰብ ነባር ባህላዊ እሴቱን ጠብቆና አጠናክሮ ለአካባቢው ሰላም መረጋገጥና ለአገር ግንባታ የድርሻውን እንዲወጣ ተጠየቀ።

የጉሙዝ ማህበረሰብ የዘመን መለወጫ "ጓንዷ" በዓል ዛሬ በአሶሳ ከተማ ተከብሯል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ወይዘሮ አለምነሽ ይባስ በበዓሉ አከባበር ወቅት እንዳሉት፤ የመተከል ዞን ሰላምን ለመመለስ ማህበረሰቡ ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረግ ይኖርበታል። 

የአሸባሪው ህወሓት ተላላኪዎች በመተከል ዞን የጉሙዝ ህዝብ ያስታጠቃቸው አስመስለው የሚያደርሱትን ጥፋት አውግዘው፤ "ቡድኑ በንጹሀን ዜጎች ላይ ያደረሰው ጥፋት በእጅጉ የሚያስቆጭ ነው" ብለዋል።

በጥፋት ድርጊቱ የጉሙዝ ማህበረሰብም ሰለባ መሆኑን አስታውሰው፤ የአሸባሪው ህወሓትና ግብረአበሮቹ ዓላማ ኢትዮጵያን ማፍረስ በመሆኑ ጉምዞች የዚህ እኩይ ዓላማ መስፈጸሚያ መሳሪያ መሆን እንደሌለባቸው አስገንዝበዋል።

አሸባሪው ህወሓት የጉሙዝ ማህበረሰብን ስም በማጠልሸት በሌላው እንዲጠላ እየሰራ በመሆኑ የማህበረሰቡ አባላት ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር ያላቸውን አንድነት በማጠናከር ቡድኑን እንዲታገሉት አፈ-ጉባኤዋ ጥሪ አቅርበዋል።

በምክንያት የሚደግፍ እና የሚቃወም ትውልድ ለማፍራት በሚደረገው ጥረት የማህበረሰቡ አባላት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል። 

የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ ወይዘሪት መስኪያ አብደላ በበኩላቸው፤  የመተከልን ህዝብ የማይወክለው ታጣቂ ቡድን የፈጸመው ጥፋት የዜጎችን አብሮነት እንደሚሸረሸር ገልጸዋል። 

ይህን ለመከላከል በዞኑ የሚገኙ የጉሙዝና ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች አንድነታቸውን ማጠናከር እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

አገርን እንደምሰሶ ደግፈው ከሚያቆሙ ጉዳዮች አንዱ ባህላዊ እሴቶች መሆናቸውን ጠቅሰው፣ “መልካም እሴቶችን ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ የሁሉም ሃላፊነት ነው” ብለዋል።

"ባህላዊ እሴቶችን ለኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ በማዋል አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመፍጠር ለሚደረገው ጥረት አስተዋጽኦ እንዲኖራቸው ማድረግ ይገባልም" ብለዋል፡

የጓንዷ የዘመን መለወጫ በዓል ተሳታፊዎች ባህላዊ እሴቶች ለአገር ሠላም፣ መረጋጋት እና ሁለንተናዊ ለውጥ መሠረት ቢሆኑም በአግባቡ እንዳልተያዙ ገልጸዋል።

ነባር ባህላዊ እሴቶች ለትውልድ እንዲተላለፉ በሚገባ ባለመሰራቱ እየተረሱ መምጣታቸውን ተናግረዋል።

 የህዝብ ጉዳቶች በማህበራዊ የትስስር ገጾች ለገቢ ምንጭነት ለማዋል የሚሯሯጡ አካላት ከድርጊታቸው ሊታቀቡ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

"ጓንዷ" ጭጋጋማው የክረምት ወቅት ተገፎ የብርሃን ወቅት የሚመጣበት ማለት ሲሆን የጉሙዝ ማህበረሰብ ብርሃን መምጣቱን ተከትሎ አዲስ ዓመቱን በተለያዩ ባህላዊ እሴቶች በደመቀ ሁኔታ ያከብራል፡፡

በዚሁ የጓንዷ በዓል አከባበር ላይ የጉሙዝ ባህላዊ ሥርዓቶች የተፈጸሙ ሲሆን ባህላዊ ዘፈኖች እና የተዘጋጁ ምግቦች ለዕይታ ቀርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም