በጋምቤላ ክልል ያለውን ሰላም በመጠበቅ ህዝቡ ልማቱን ማጠናከር አለበት—አቶ ጋትሉዋክ ቱት

1868

ጋምቤላ ነሀሴ 8/2010 በጋምቤላ ክልል ያለውን ሰላም በመጠበቅ ለተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች መሳካት ህዝቡ ድጋፉን ማጠናከር እንዳለበት የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር  ጋትሉዋክ ቱት አሳሰቡ።

ርዕሰ መስተዳደሩ ለኢዜአ እንደገለጹት ባለፉት ሁለት ዓመታት በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የጸጥታ ችግር የነበረ ቢሆንም በክልሉ ህዝብና መንግስት የጋራ ጥረት የአካባቢው ሰላም ተጠብቆ ቆይቷል።

በአሁኑ ወቅት እንደሀገር እየመጣ ያለው የሰላም ፣የአንድነት፣ የፍቅርና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ በመደገፍ የክልሉን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ህዝቡ እገዛውን ማጠናከር አለበት፡፡

“የክልሉ መንግስት በተያዘው የበጀት ዓመት የአካባቢውን ሰላም ይበልጥ በማጠናከር የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን በማፋጠን ህዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ  በትኩረት እየሰራ ይገኛል “ብለዋል።

ሀገራዊ ለውጡ በአሳሳቾች እንዳይደናቀፍ እንደ ክልል በሶስቱ የብሄረሰብ ዞኖች የግንዛቤ ማስጨበጫ የሰላም ኮንፈረንስ መካሄዱንም አመላክተዋል።

በቀጣይም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚሳተፉበት የሰላምና የልማት ህዝባዊ ኮንፈረንስ እንደሚካሄድም ነው ርዕሰ መስተዳደሩ የገለጹት።

የክልሉን ሰላም ጠብቆ እንደሀገር የመጣውን ለውጥ በማስቀጠል የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ስኬት ህዝቡ ጠንክሮ እንዲሰራም አሳስበዋል፡፡

ከጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ ኡዶል አግዋ  በሰጡት አስተያየት “የሰላም እጦት የሚፈጥረውን ችግር የክልሉ ህዝብ ጠንቅቆ ያውቃል” ብለዋል።

ሰላም በሌለበት ዴሞክራሲን፣ ልማትንና  ፍትህዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ  እንደማይቻል ጠቁመው እየመጣ ያለውን ለውጥ እንዲቀጥል የአካባቢውን ሰላም ህዝቡ ነቅቶ መጠበቅ እንደሚገባ አመልክተዋል።

“ሰላምን የመጠበቁ ስራ የአንድ አካል ሳይሆን የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ነው “ያሉት ደግሞ ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ኃይለማሪያም ተክለማሪያም ናቸው።

በእሳቸው በኩልም ከክልሉ መንግስት ጎን በመሰለፍ በአካባቢው ያለውን  ሰላም ለማስጠበቅ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡

አቶ ዘመድአገኘሁ ጋረድ የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው ሰላምንና አዲሱን  ለውጥ ለማስቀጠል የሚደረገውን  ጥረት እንደሚደግፉ ገልጸዋል፡፡