በአዋሽ ተፋሰስ ላይ ሁለት ግድቦችን ለመገንባት የመንግስትን ይሁንታ እተጠበቀ ነው

71
አዲስ አበባ ነሀሴ 8/2010 በአዋሽ ተፋሰስ ላይ ሁለት ግድቦችን ለመገንባት የመንግስትን ይሁንታ እየጠበቀ መሆኑን የአዋሽ ተፋሰስ ባለስልጣን ገለፀ። ግድቦቹ በአካባቢው የሚያጋጥሙትን የጎርፍ አደጋና የውሃ አጥረት ከመከላከል ባሻገር የመስኖ እና ዓሣ ልማትን ጨምሮ ሌሎች ሁለገብ አገልግሎቶችን ይሰጣሉ ተብሏል። ለግድቦቹ ግንባታ 11 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ከሁለት ዓመት በፊት የወጣ መረጃ ያመለክታል። በባለስልጣኑ የውሃ ኃብት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ሽፈራው ደምሴ እንደተናገሩት፤ ግድቦቹ የሚገነቡት በታችኛው አዋሽ አካባቢ በሎጊያ ወንዝ እና በመካከለኛው አዋሽ፤ አዋሽ ብሄራዊ ፓርክ አካባቢ ነው። ግድቦቹ በአካባቢው የሚያጋጥሙትን የጎርፍ አደጋና የውሃ አጥረት ከመከላከል ባሻገር የመስኖ እና ዓሣ ልማትን ጨምሮ ሌሎች ሁለገብ አገልግሎቶችን ይሰጣሉ ብለዋል። በሎጊያ ወንዝ ላይ የሚገነባው ግድብ እስከ 500 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሊትር ውሃ የመያዝ አቅም እንደሚኖረው የተናገሩት አቶ ሽፈራው አዋሽ ብሄራዊ ፓርክ አካባቢ የሚገነባው ግድብ ዲዛይን ላይ ለውጥ የሚደረግ በመሆኑ ግደቡ የሚይዘውን የውሃ መጠን ለመናገር አዳጋች መሆኑን ጠቁመዋል። ግድቦቹ ለግንባታ ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚያስፈልጋቸውና የመንግስትን የበጀት ውሳኔ እንደሚጠይቁም ገልፀዋል። ግድቦቹን ለመገንባት የሚያስችለው ጥናት ተጠናቆ  የበጀት ውሳኔ እንዲሰጥበት ከአንድ አመት በፊት ለመንግስት መቅረቡን ገልጸዋል። ሆኖም ግን እስካሁን በመንግስት በኩል የተሰጠ ምላሽ እንደሌለ አቶ ሽፈራው አስታውቀዋል። የግድቦቹ መገንባት በተፋሰሱ አካባቢ በበጋ ወቅት የሚከሰትን የውሃ እጥረት እና በክረምት ወቅት ሊያጋጥም የሚችልን የጎርፍ ስጋትን ለመቀነስ ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል ተብሏል። በ2008 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ለሁለቱ ግድቦች ግንባታ ማስፈጸሚያ 11 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በጀት እንደሚያስፈልግ ተገልፆ የነበረ ሲሆን  ግንባታቸውም ባለፈው ዓመት ይጀመራል ተብሎ የነበረ ቢሆንም እስካሁን ግን የተጀመረ ነገር የለም።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም