የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባዔ የበላይ ጠባቂ አባቶች መልእክት ከታላቁ ሕዳሴ ግድብ

113

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5 ቀን 2013 (ኢዜአ)የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባዔ የበላይ ጠባቂ አባቶች በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በመገኘት የግንባታውን ክንውን ተመልክተዋል፤ ለኢትዮጵያና ህዝቦቿም በሥፍራው ፀሎት አድርሰዋል።

በጉብኝታቸው የእያንዳንዱ ቤተ-እምነት ተወካይ አባቶችም በበዓሉ ዋዜማ በግድቡ ግንባታ ሥፍራ ላይ መልእክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የፓትሪያርኩ ልዩ ጽህፈት ቤትና የውጭ ጉዳይ የበላይ ኃላፊ ብፁዕ ዶክተር አቡነ አረጋዊ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ በኢትዮጵያውያን እውቀት፣ ጉልበትና ሃብት የሚገነባ የትውልዱ አሻራ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያዊያን የአንድነታቸው፣ የድላቸው፣ የልማትና ብልጽግና ተምሳሌት የሆነ የነገ ብርሃን ፋና ፕሮጀክት መሆኑንም ነው የገለጹት።

የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ወንዙን በብቸኝነት ሲጠቀሙት እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ላይ ኢትዮጵያ በወንዙ ዙሪያ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲሰፍን የምታራምደው አቋም ትክክል መሆኑን አንስተዋል።

"ሰጭ ይመሰገናል እንጂ አይኮነንም" ያሉት ብጹዕ አቡነ አረጋዊ፤ ከዚህ አኳያ ግብጽና ሱዳን ኢትዮጵያ ከወንዟ ልጠቀም በማለቷ ሊከፉ አይገባም ብለዋል።

ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች የዑለማ ምክር ቤት አባል ሸህ መሃመድ ሲራጅ በበኩላቸው፤ በሥፍራው ተገኝተው ግድቡ የደረሰበትን ደረጃ ማየታቸው እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል።

ግድቡ የደረሰበት ደረጃ የኢትዮጵያ ትንሳኤ ቅርብ መሆኑን አመላካች እንደሆነ ገልጸው፤ በአዲሱ ዓመትም ያለፈውን ዓመት ችግሮች በመተው በሥራና በጸሎት ለተሻለ ዘመን እንዲሆን መትጋት አለብን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ እና የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ህብረት ፕሬዝዳንት ፓስተር ጻድቁ አብዶ በተመሳሳይ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።

ግድቡ የኢትዮጵያዊያን የሕልውና መሰረት ነው ያሉት ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ፤ ኢትዮጵያ ውሃዋን ለሌሎች ስታጋራ እንደቆየች ሁሉ ከግድቡ የምታመነጨውን ኃይል ለሌሎች ለማጋራት ፍላጎት እንዳላት ተናግረዋል።

በዘመናት ቅብብሎሽ ኢትዮጵያን ያስተዳደሩ መንግስታት ሌሎችን ለመጉዳት አስበው እንደማያውቁ የተናገሩት ፓስተር ጻድቁ፤ ከዚህ አኳያ የሕዳሴ ግድብ የትብብር እንጂ የጸብ መነሻ መሆን እንደሌለበት ገልጸዋል።

የ2014 አዲስ ዓመትም የሰላም፣ የበረከት፣ የደስታ፣ የብልጽግና፣ የዕድገትና የፍቅር እንዲሆን አባቶች መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም