በንጹኃን ዜጎች ላይ ጭፍጨፋ የሚፈጽመውን የሕወሃት አሸባሪ ቡድን ማጥፋት አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው

96

ጳጉሜ 05 ቀን 2013 (ኢዜአ) ንጹሃን ዜጎች ላይ ጭፍጨፋ የሚፈጽመውን የሕወሃት አሸባሪ ቡድን ማጥፋት አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን የምድር ኃይል ምክትል አዛዥ ሜጀር ጀኔራል እንዳልካቸው ወልደኪዳን ገለጹ።

የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት አዋሽ አርባ ውጊያ ቴክኒክ ትምህርት ቤት በመሰረታዊ ወታደርነት ያሰለጠናቸውን ወታደሮች አስመርቋል።

የምድር ኃይል ምክትል አዛዥ ሜጀር ጀኔራል እንዳልካቸው ወልደኪዳን በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ አሸባሪው ህወሃት የሽብር ድርጊቱን አጠናክሮ ቀጥሎበታል።

ለአብነትም በማይካድራ፣ ጋሊኮማና በሌሎችም ኃይል በያዛቸው አካባቢዎች በንጹኃን ላይ ያደረሰው ጭፍጨፋ የቡድኑን ከትናንት የቀጠለ የአረመኔነት ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

ቡድኑ የሕዝብን ንብረት በመዝረፍ፣ በማውደም አርሶ አደሩ ለሞትና ለስደት መዳረጉንም ጠቁመዋል።

አሸባሪና ወራሪው ቡድን ካልጠፋ የአገር ሰላምና እድገት አይታሰብም ያሉት ሜጀር ጀኔራሉ፤ ቡድኑ ከምድረ ገጽ ማጥፋት አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።

ተመራቂዎቹም ይህንን የጥፋት ኃይል ሙሉ ለሙሉ ለማጥፍት በወርቃማ ጊዜ ወታደራዊ ጥበብን በመቅሰም ለምርቃት መብቃታቸው የሚያኮራ መሆኑን ተናግረዋል። 

የአዋሽ አርባ ውጊያ ቴክኒክ ትምህርት ቤት ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ተመስገን አቦሴ፤ ተመራቂዎቹ መሰረታዊ የውትድርና ሥልጠና መቅሰማቸውን ጠቁመዋል።

ተመራቂዎችም ተለዕኳቸውን በመፈጸም ለኢትዮጵያዊን የድል ዜና ለማብሰር ዝግጁ መሆናቸውንም ነው የተናገሩት።

ተመራቂዎቹ በአዋሽ አርባ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤትና በአዋሽ ጥምር ጦር አካዳሚ ሥልጠናቸው ሲከታተሉ ቆይተዋል።

በምርቃት ሥነ-ሥርዓቱ ከፍተኛ የጦር መኮንኖችና ሌሎች የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም