የአዋሽ ተፋሰስን የውሃ ጥራት ለመከታተል ሳይንሳዊ መረጃ መያዣ ቋት ሊቋቋም መሆኑ ተገለፀ

119
አዲስ አበባ ነሀሴ 8/2010 የአዋሽ ተፋሰስን የውሃ ጥራት ለመከታተል የሚያስች የተፋሰሱን ሳይንሳዊ መረጃ የሚይዝ የመረጃ ቋት ማዕከል ሊቋቋም ነው። በተፋሰሱ መረጃውን የሚያሰባስብ ቴክኖሎጂና ሶፍትዌር የሚጠቀም ዘመናዊ የአካባቢ መቆጣጠሪያ ዘዴ ተግባር ላይ እንደሚውልም ተጠቁሟል። የአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር ከህንድ የሳይንስና አካባቢ ማዕከል ጋር በመተባባር የቴክኖሎጂውን አጠቃቀም  በተመለከተ ለባለሙያዎች ስልጠና እየሰጠ ነው። የህንድ የሳይንስና አካባቢ ማዕከል ምክትል ዳይሬክተር ቻንድራ ሁሻን እንዳሉት፤ ማዕከሉ ተፋሰሱን አስቀድሞ መቆጣጠር የሚያስችል ቴክኖሎጂና ሶፍትዌር በመጠቀም ሳይንሳዊ መረጃዎችን ለማሰባሰብና ለመተንተን የሚያስችል ነው። በአካባቢ ብክለት በመቆጣጠር ሂደት ትልቁ ችግር ሳይንሳዊ መረጃ አለመኖሩ መሆኑን ገልፀው ማዕከሉ በኢትዮጵያ አዋሽ ተፋሰስ የወንዝ ጥራት ቁጥጥር ለመስራት ቴክኖሎጂና ሶፍትዌር ይጠቀማል ብለዋል። በቴክኖሎጂው ላይ ለአንድ ወይም ለሁለት አመት የክትትል ስራ ከተሰራ በኋላ ወንዙ በተለያዩ ወቅቶች የሚኖረውን የውሃው ጥራት በመለየትና በመተንተን የመቆጣጠሪያ እቅድ የሚዘጋጅ መሆኑን አመልክተዋል። በአንድ አመት ውስጥ ቴክኖሎጂውን የማላመድና የማሰልጠን ስራ እንደሚሰሩ ገልፀዋል። በአዋሽ ተፋሰስ ባለስልጣን የውሃ ሀብት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ሽፈራው ደምሴ ተፋሰሱ በአካባቢ ተፅዕኖ ምክንያት በበጋ ለውሃ እጥረት በክረምት ደግሞ ለውሃ ሙላት እንደሚጋለጥ ገልፀዋል። ባለስልጣኑ የክረምትን ውሃ በመያዝ ማልማት፣ የውሃ ጥራት ቁጥጥር፣ የተቀናጀ የተፋሰስ እንክብካቤ፣ የጎርፍና የድርቅ መከላከል እቅድ  አዘጋጅቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረው ቴክኖሎጂው ስራውን እንደሚያጠናክር ጠቁመዋል። ቴክኖሎጂውን በመጠቀም ወንዙን ተከትሎ የት ላይ ምን አይነት የብክለት ምንጭ እንዳለ እና እንዴት መከታተል እንደሚቻል አስረድተዋል። ከዚህ በፊትም የአዋሽ ወንዝን ተከትሎ በየወሩ ናሙናዎች የሚወሰድባቸው 17 የናሙና መውሰጃ ቦታዎችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የማስደገፍ ስራ እንደሚሰራ ገልጸዋል። ናሙና የሚወሰድባቸው ቦታዎች በመረጃ መረብ እንዲተሳሰሩ ተደርጎ ሁሉም የሚሰበሰብ መረጃ ወደአንድ ማዕከል እንዲቀመጥ የሚያስችል የመረጃ ቋት ማዕከል ይመሰረታል። በስልጠናው ከናይጀሪያ፣ ጋና፣ ግብፅ፣ ዛንዚባርና ስዋዚላንድ የተውጣጡ ባለሙያዎች አቅምን መገንባት የሚያስችል የልምድ ልውውጥ ያደርጋሉ። የአዋሽ ተፋሰስ የአዋሽ ወንዝንና ገባሮቹን የያዘ ሲሆን በተፋሰሱ አካባቢ የአገሪቱ 10 በመቶ ህዝብ ይኖራል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም