የአሸባሪውን እኩይ ሴራ ለማክሸፍ በአፋር ክልል የጸጥታ መዋቅሩ እየተጠናከረ ነው

83

ሰመራ፣ ጷጉሜ 03 ቀን 2013 (ኢዜአ) የአሸባሪውን ህወሃት እኩይ ሴራ እስከመጨረሻ ለማክሸፍ በአፋር ክልል የጸጥታ መዋቅሩን የማጠናከር ስራ በየደረጃው እያከናወነ እንደሚገኝ የክልሉ ሚሊሻ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

ሶስት ወንድማማቾችን ጨምሮ በክልሉ የሰለጠኑ የሚሊሻ አባላት ዛሬ በሰመራ - ሎግያ ከተማ ተመርቀዋል።

የሚሊሻ ጽህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ አይዳሂስ አፍኬኤ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ አሸባሪው ህወሃት ኢትዮጵያን ለማፍረስ አልሞ የከፈተውን ጦርነት ለመቀልበስ የአፋር ህዝብ እንደወትሮው ሁሉ ዝግጁ ነው።

ቡድኑ አፋርን እንደመሸጋገሪያ ተጠቅሞ የአገሪቱን ገቢና ወጪ መስመር በመዝጋት የህልውና አደጋ ለመጣል ያደረገው ሙከራ በህዝቡና በጸጥታ መዋቅሩ የተባበረ ክንድ መክሸፉን ተናግረዋል።

የአፋር ህዝብ ከአገር መከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የጸጥታ ሃይሎች  ጋር በመቀናጀት ያደረገው ጥረት ውጤት ማምጣቱን ገልጸዋል።


የክልሉ መንግስት የአሻበሪውን ህወሃት እኩይ ሴራ እስከመጨረሻ ለማክሸፍ የጸጥታ መዋቅሩን እያጠናከረ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

ዛሬ የተመረቁት የሚሊሻ አባላት የህዝባቸውን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ  ስነ-ምግባር የተሞላበት የህግ ማስከበር ስራቸውን በአግባቡ እንደሚወጡ የገለጹት ሃላፊው፤ በተለያዩ ወረዳዎች ስልጠና እየወሰዱ የሚገኙ ከ7 ሺህ በላይ ተጨማሪ ሚሊሻዎች ስልጠናቸውን በብቃት አጠናቀው በዚህ ሳምንት እንደሚመረቁ ጠቁመዋል።

የሠመራ - ሎጊያ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አሊ መሀመድ በበኩለቸው፤ "አሸባሪው ህወሃት የከፈተብን ጦርነት ከመመከቱ በተጓዳኝ የአካባቢያችንን ሠላም ማስጠበቅ ተቀዳሚ አጀንዳችን ነው" ብለዋል።

ከተማ አስተዳደሩ ከሚሊሻ ጽህፈት ቤት ጋር በመተባበር ያሰለጠናቸው የሚሊሻ አባላት የህዝቡን ደህንነት ለማስጠበቅ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖራቸው ገልጸዋል።

ተመራቂዎቹ በሰጡት አስተያየት አሸባሪው ቡድን የፈጸመውን ወረራ ለመቀልበስና ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ዝግጁነታቸውን ገልጸዋል።

በቀጣይ በየትኛውም ቀጠና የሚሰጣቸውን ግዳጅ ለመወጣት ያላቸውን ዝግጁነት አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም