ብሔራዊ የመረጃና ደህንነት ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በቪአይፒ እና በቁልፍ መሰረተ ልማት ጥበቃ ያሰለጠናቸውን የሪፐብሊካን ጋርድ አባላት አስመረቀ

154

ጳጉሜን 3/2013 (ኢዜአ) በብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ስር የሚገኘው ብሔራዊ የመረጃና ደህንነት  ዩኒቨርሲቲ  ኮሌጅ  ከሪፐብሊካን ጋርድ  የተመለመሉ  በቪአይፒ  እና  በቁልፍ  መሰረተ  ልማት  ጥበቃ  የሰለጠኑ መኮንኖችን  አስመርቋል ፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ተመስገን ጥሩነህ በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት የሪፐብሊካን ጋርድ  አባላት ትልቅ ሃላፊነትና እምነት የተጣለባቸው ሲሆን፤ የሀገርን ብሔራዊ ደህንነት በማረጋገጥ ረገድም ከፍተኛ ሚና ሲያበረክቱ  እንደነበር  ገልጸዋል፡፡

በተለይ ከሀገራዊ ለውጡ ጋር ተያይዞ ያጋጠሙ ፈተናዎችን በከፍተኛ ወኔና ትዕግስት በመፍታት ያበረከቱት አስተዋጽኦ አስቸጋሪ ጊዜዎችን ለማለፍ  እንዳስቻለ  ያስታወሱት  አቶ ተመስገን፤በቀጣይ ተልዕኳቸውን በብቃትና ጥብቅ በሆነ የስራ ዲሲፒሊኒ ለመወጣት የሚስችላቸውን ስልጠና ከዩኒቪርሲቲ ኮሌጁ መቅሰማቸውን አመልክተዋል፡፡

አቶ ተመስገን የሪፐብሊካን ጋርድ አባላቱ ተጨማሪ አቅም የሚፈጥርላቸውን ስልጠና እንዲያገኙ ላስቻሉት ለዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ አካለት ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል፡፡

በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የሪፐብሊካን ጋርድ  ምክትል አዛዥ ብ/ጀነራል አብድሮ ከድር፤የሪፐብሊካን ጋርድ አባላት በርካታ ሀገራዊ ግዳጆችን እየተወጡ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ አሁንም አሸባሪው ህወሓት በተለያዩ አቅጣጫዎች የከፈተውን ጦርነት ለመመከት ከሌሎች ሃይሎች ጋር በመቀናጀት ከፍተኛ ጀብዱ እየፈጸሙ ነው ብለዋል፡፡

‹‹በብሔራዊ የመረጃና ደህንነት ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የተሰጠው ስልጠና ሀገራችን ከእኛ  የምትጠብቀውን ግዳጅ በላቀ ደረጃ ለመፈጸም እገዛ ያደርጋል›› ያሉት ብ/ጀነራል አብድሮ፤ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎትና የዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ አመራሮች ስልጠናው ከውጥኑ ጀምሮ እስከ ፍጻሜው የተሳካ እንዲሆን ከፍተኛ እገዛ በማድረጋቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ ከልጠናውም  የሪፐብሊካን ጋርድ አባላቱ ለተሰጣቸው ስምሪት አጋዥ የሚሆን በጣም ጠቃሚ ግብዓት መገኘቱን መስክረዋል፡፡

የብሔራዊ የመረጃና ደህንነት ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ፕሬዚዳንት አቶ ወንድወሰን ካሳ በበኩላቸው፤ የሪፐብሊካን ጋርድ አባላት ከተሰጣቸው ሀገራዊ ተልዕኮ አንጻር ውጤታማ ስምሪት እንዲያደርጉ የሚያስችላቸው ስልጠና እንደተሰጣቸው አመልክተዋል፡፡

የቪአይፒ እና የቁልፍ መሰረተ ልማት  ጥበቃ የዘመናችን የብሔራዊ ደህንነት ስምሪት ወሳኝ አካል ናቸው ያሉት የዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ፕሬዚዳንት፤ የሪፐብሊካን ጋርድ አባላቱ በዚህ ረገድ አቅማቸውንና ክህሎታቸውን የሚያሳድግ የንድፈሀሳብና የተግባር ስልጠና መውሰዳቸውን አመልክተዋል፡፡

የብሔራዊ የመረጃና ደህንነት ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በ2013 በጀት ዓመት ለአገልግሎት መስሪያ ቤቱ ጀማሪ ኦፊሰሮች ከሰጠው ተከታታይ ስልጠና በተጨማሪ፤ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ፣ለገቢዎችና ጉምሩክ፣ለክልሎች እንዲሁም ለተለያዩ ተቋማት ባለሙያዎችና አመራሮች  በመረጃ፣ በደህንነትና በተያያዥ መስኮች በርካታ ስልጠናዎች ስጥቷል፡፡ በቀጣይም ለአካባቢው እና ለጎረቤት ሀገራት አቻ የመረጃና ደህንነት ተቋማት በመረጃና ደህንነት ዘርፎች የተለያዩ ስልጠናዎችን ለመስጠት ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ስምምነት መፈፀሙን የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ያደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም