ኢትዮጵያን በማሪታይም ኢንዱስትሪው ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው....ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ

155

ባህርዳር  ጳጉሜን 3/2013 (ኢዜአ) ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የማሪታይም አካዳሚ ተመራቂዎች ለሥራ በሚሄዱባቸው ሀገራት ሥራቸውን በጥራትና በታማኝነት ከማስራት ባለፈ የሀገራቸው አምባሳደር መሆን እንዳለባቸው የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት አሳሰቡ።

 የዩኒቨርሲቲው ማሪታይም አካዳሚ ለ18ኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን 22 ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል።

ፕሬዚዳንቱ ዶክተር ፍሬው ተገኘ በምረቃ ስነ-ስርአቱ ላይ እንዳሉት ተማሪዎች በቆይታቸው ዓለም አቀፋዊ ትምህርትና ሙያዊ ስነ-ምግባርን የተላበሰ ስልጠና አግኝተዋል።

ተመራቂዎቹ ለሥራ በሚሰማሩባቸው የዓለም ሀገራት ስራቸውን በጥራትና በሃላፊነት እንዲሁም ሙያዊ ስነ-ምግባርን ተላብሰው በማከናወን ሀገራቸውንና እራሳቸውን ማስመገን ይገባቸዋል።

"ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ የፕሮፖጋንዳ ጦርነት ሰለባ ሁናለች" ያሉት ፕሬዝዳንቱ፣ ተመራቂዎቹ በሙያቸው ውጤታማ ከመሆን ባለፈ ለአገራቸው አምባሳደር ሆነው እንዲያገለግሉ አሳስበዋል።

በመላው ዓለም የሃገራቸው አምባሳደር የሚሆኑ ብቁ የማሪታይም ባለሙያዎችን በማፍራት ሃገርንና ወገንን ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

"በየሄዱበት የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ በማስረዳት እውነታውን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የማሳወቅ ተጨማሪ ሀገራዊ ሃላፊነትን መወጣት ይኖርባችዋል" ብለዋል።

የማሪታይም አካዳሚው ኮማንዳንት ካፒቴን ቻርል ኮትዚ በበኩላቸው ተመራቂዎቹ የንድፈ ሃሳብና የተግባር ስልጠናዎችን በበቂ ሁኔታ መውሰዳቸውን ገልጸዋል።

ካፒቴን ቻርል እንዳሉት ተመራቂዎቹ በኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያገኙ ሲሆን በእዚህ ስልጠናም ለስድስት ወር የንድፈ ሃሳብና የተግባር ትምህርት ተከታትለው የመርከብ ኤሌክትሪካል ኦፊሰርነት ሙያን አዳብረው የተመረቁ ናቸው።

ትምህርቱ በጥራትና ዓለም አቀፍ መስፈርትን ባሟላ መልኩ የተሰጠ መሆኑን ካፒቴኑ ገልጸው፣ መመረቅ ብቻ በራሱ ግብን እንደማይሆን ጠቁመዋል።

ተመራቂዎቹ ወደ ፊት ለሥራ በሚሰማሩባቸው ሀጋራት ሁሉ የሚገጥማቸው ፈተናዎችን በመወጣት የተማሩትን ትምህርት በተግባር እንዲያሳዩ አስገንዝበዋል።

በዛሬው እለትም የተግባርና የንድፈ ሃሳብ ትምህርቱን ተከታትለው በብቃት ማጠናቀቅ የቻሉ 22 ሰልጣኞች ተመርቀዋል።

በተግባርና በንድፈ ሃሳብ የታገዘና ዓለም አቀፍ ጥራትን የተላበሰ ትምህርት ማግኘታቸውን የገለጸው ደግሞ ተመራቂ ተሚ አበበ ነው።

የተሰጣቸው ትምህርት ከአካዳሚያዊ እውቀት ባለፈ ስነ-ምግባርንና የግል ስብዕናን በመገንባት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳበረከተለት ተናግሯል።

በቀጣይ በስራ ዓለም ሊገጥሙ የሚችሉ ፈተናዎችን ተቋቁሞ በሚሰማራባቸው ሀገራት ሁሉ ራሱንና  ሀገሩን ለመጥቀም ተግቶ እንደሚሰራ ተናግሯል።

ስልጠናው ኢትዮጵያ እንደ አዲስ እያቋቋመች ላለችው የባህር ሃይል አቅም የሚሆንና በቂ እውቀት እንዳገኘበት የገለጸው ደግሞ ጁኔየር ሊፍተናንት እዮብ ዘለቀ ነው።

ቀደም ሲል ከሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ በኤሌክትሮ ሚካኒካል ምህንድስና የመጀመሪያ ዲግሪ ማግኘቱን ገልጾ፣  

በእዚህ ስልጠናም ባህር ሃይልን ለማዘመን የሚያስችል እውቀት መቅሰሙን ተናግሯል።

በምረቃ ስነ-ስርአቱ ላይ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ የማሪታይም አካዳሚው መምህራኖች እና የተመራቂ ቤተሰቦች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም