ዘላቂ የሆነ ምርታማነት እንዲረጋገጥ ሳይንሳዊ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና አጠቃቀም ስራ ማጠናከር ይገባል---የእርሻና እንስሳት ሀብት ሚኒስቴር

111
አዳማ ነሀሴ 8/2010 ዘላቂ የሆነ የምርትና ምርታማነት እድገት እንዲረጋገጥ ሳይንሳዊ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና አጠቃቀም ስራን ማጠናከር እንደሚገባ ተመለከተ። ሀገር አቀፍ የ2010 ዓ.ም. የተፈጥሮ ሀብት ዘርፍ እቅድ አፈፃፀምና የቀጣይ ዘመን አመላካች እቅድ  የምክክር መድረክ  ትናንት በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው። የእርሻና እንስሳት ሀብት ሚንስትር ዴኤታ ዶክተር ካባ ዑርጌሳ እንደገለጹት የግብርና ዘርፉ እድገት የዜጎችን የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባሻገር የአግሮ ፕሮሰስንግ ዘርፍ አስተማማኝ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በዚህም ዘላቂ የሆነ የምርታማነት እድገት እንዲረጋገጥ ሳይንሳዊ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና አጠቃቀም ስራ ማጠናከር  እንደሚገባ አመልክተዋል። ይህንኑ መሰረት በማድረግ የተፋሰሶች ልማት ሥራ ሳይንስን ማዕከል ባደረገ መልኩ የውሃ ሀብት አያያዝና አጠቃቀም ፣ የአፈር ለምነትና የመሬት አጠቃቀም ማሻሻል በቀዳሚነት ማከናወን ተገቢ ነው። ለሥራው ውጤታማነት በየደረጃው የሚገኙ የዘርፉ ምሁራን፣ተመራማሪዎች፣ አመራሮች ፣አርሶና አርብቶ አደሮች ከእቅድ ጀምሮ በማሳተፍ ፣ ክህሎትና ግንዛቤውን ለማሳደግ ርብርብ ማድረግ ይገባል። ባለፈው የበጀት ዓመት ህብረተሰቡን በማሳተፍ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና እንክብካቤ ሳይንሳዊ ይዘትን በተከተል አካሄድ 3 ሚሊዮን በሚጠጋ ሄክታር መሬት ላይ መሰራቱ ተጠቅሷል። ባለፉት ዓመታት በሀገር ደረጃ በተከናወኑ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራዎች የግብርና ዘርፍ እድገት ባለ ሁለት አሃዝ እድገት እንዲያስመዘግብ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩም ተመልክቷል፡፡ የተመረጡ 5ሺህ 770 ተፋሰሶችን መሰረት በማድረግ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ የአፈርና ውሃ እቀባ፣የጠረጴዛ እርከን፣የችግኝ ተከላና ሌሎችም የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራዎች በክልሉ መከናወኑን የገለጹት ደግሞ የኦሮሚያ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ምክትል ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ዱጉማ ናቸው። ህብረተሰቡ በክልሉ የነበረውን ወቅታዊ የፀጥታ ችግር በመቋቋም የተፈጥሮ ሀብት ልማትና እንክብካቤ ሥራን በ6ሺህ 447 የገጠር ቀበሌዎች ላይ ማከናወኑን ጠቅሰው በዚህም ከ3 ሚሊዮን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች መሳተፋቸውን ተናግረዋል። በክልሉ በሰው ሰራሽና ተፈጥሮ አደጋ የተጎዱ  አካባቢዎች እንዲያገግሙ በማድርግ በኩልም ከ640ሺህ ሄክተር በላይ መሬት ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ  ነፃ መደረጉንም ጠቁመዋል። የደቡብ ህዝቦች ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ተወካይ አቶ ሙሐመድ ኑር ፋሪስ በበኩላቸወ ህብረተሰቡ በተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ንቁ ተሳትፎ እንዲኖረውና ከዘመቻ ባለፈ በመደበኛነት ዓመቱን ሙሉ እንዲያከናውን ባለፈው የበጀት ዓመት ጥረት ሲደረግ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ በዚህም ከ1 ሚሊዮን በላይ ህዝብ በተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ላይ  በማሳተፍ በ412 ሺህ ሄክታር ላይ ሳይንሳዊ የአፈርና ውሃ እቀባ፣የጠረጴዛ እርከን ሥራዎች ተከናውነዋል። አቶ ሙሐመድ ኑር እንዳሉት በበጀት ዓመቱ ከ10ሺህ በላይ ሄክታር የለሙ ተፋሰሶች ለሥራ አጥ ወጣቶች ተላልፏል። በምክክር መድረኩ በኦሮሚያ፣ደቡብ ፣አማራና ትግራይ ክልሎች የተፈጥሮ ሀብት ልማት፣የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ዙሪያ በበጀት ዓመቱ የተከናወኑ ሥዎች ቀርበው ውይይት እየተደረገባቸው ነው፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም