አሸባሪው ሕወሓት በሚፈጽማቸው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ትክክለኛ አሸባሪ መሆኑን አስመስክሯል

51

ጷጉሜ 03 ቀን 2013 (ኢዜአ) አሸባሪው ሕወሓት በሚፈጽማቸው ኢ-ሕገ-መንግሥታዊና ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች ትክክለኛ አሸባሪ መሆኑን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በተግባር ማስመስከሩን የመከላከያ ሚኒስቴር ገለጸ።

የመከላከያ ሚኒስቴር ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመሆን መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ከተማ ካደረጉና ከተለያዩ ኤምባሲዎች ለተውጣጡ ወታደራዊ አታሼዎች በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ ሰጥቷል።

የመከላከያ ሚኒስትር ዶክተር ቀንአ ያደታ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ አሸባሪው ሕወሓት ከምሥረታው ጀምሮ ኢትዮጵያን ለማፍረስ እኩይ ዓላማ ያነገበ ቡድን ነው።

ቡድኑ ሥልጣን ላይ በቆየበት 27 ዓመታት አገሪቷን ለማፍረስና ለማዳከም በተቋም ደረጃ ጭምር ፖሊሲና ስትራቴጂ ቀይሶ ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል።

በአገሪቷ የሚስተዋለውን የብሔር ግጭት እየቀሰቀሰ ግጭትን ለህልውናው ማራዘሚያ የሚጠቀም መሆኑን አብራርተዋል።

ቡድኑ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ በሆነ መልኩ ባዋቀረውና  የ"ትግራይ መከላከያ ኃይል" ብሎ በሰየመው ታጣቂ አማካኝነት ጦርነቱን ወደ አማራና አፋር ክልሎች ያስፋፋው ለሽብር ዓላማው መሆኑን ጠቁመዋል።

ይህንንም ተከትሎ በአገሪቷ በተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋሉት መፈናቅሎችና ሌሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች አሸባሪው ቡድን ያመጣቸው ችግሮች መሆናቸውን አብራርተዋል።

"በዚህም ትክክለኛ ሽብርተኛ ቡድን መሆኑን ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ አስመስክሯል" ብለዋል።  

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናታን ተስፋዬ፤ ቡድኑ ማኅበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ እያሳሰተ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ያም ብቻ ሳይሆን በመደበኛ የመገናኛ ብዙሃንም የውሸት ምስሎችን ጭምር በመጠቀም የተሳሳተ መረጃዎችን ፈጥሮ ለማሳሳት እንደሚጥር ተናግረዋል።

ይህንን ሐሰት ላይ የተመሰረተ የማኅበራዊ ሚዲያና የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ዘመቻ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ መገንዘብ እንዳለበት ጠቁመው፤ ትክክለኛውን መረጃ ማጣራት እንደሚገባ አስረድተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ለተከሰቱት ችግሮች ሁሉ አሸባሪው ቡድን ምክንያት መሆኑን አስረግጠው አስገንዝበዋል።

የቡድኑን ጠብ አጫሪነት ባህሪ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተረድቶ ተገቢውን የአጋርነት ድጋፍ ለኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

የመከላከያ ሚኒስቴር የውጪ ግንኙነት ዳይሬክተር ብርጋዴር ጀኔራል ቡልቲ ታደሰ፤ አሸባሪ ቡድኑ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለቀጣናውም ስጋት መሆኑን በመገንዘብ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰቡ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጎን በመቆም አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

ወታደራዊ አታሼዎቹ ለተሰጣቸው ማብራሪያ አመስግነው፤ ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ችግር በቅርቡ ወደ ቀደመ ሰላሟ እንደምትመለስ ያላቸውን እምነት ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም