የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ቀመር ከሌላው ዓለም አቆጣጠር በስሌትም ሆነ በትርጉም የተለየ ነው

329

ጷጉሜ 03 ቀን 2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ቀመር በሌላው ዓለም ከሚገኘው የዘመን አቆጣጠር በስሌትም ሆነ በትርጉም የተለየ ነው፡፡

የዩሊዮስ ብሎም የጎርጎሪዎስ የዘመን ቀመሮች ታሪክን ታሳቢ ያደርጋሉ፡፡

በኢትዮጵያ በአንድ ዘመን ውስጥ የሚገኙ ወራቶች የየራሳቸው የሆኑ ትርጓሜዎችን ይዘዋል፡፡ 

በሰዋሰው ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ኮሌጅ የአንድምታ ትርጓሜ መምህር መጋቢ ሃዲስ ስቡህ አዳምጤ ኢትዮጵያ ከብሉይ ዘመን በፊት ዓመታትን ትቆጥር እንደነበር ገልጸዋል።

“ከክርስቶስ ልደት በፊት በብሉይ ኪዳን የነበረውን 5 ሺህ 500 ዘመን እንደገና ከክርስቶስ ልደት በኋላ ያለውን ደምረን ዓመተ ዓለሙን በዚያ ቀመሩን እናወጣለን” ብለዋል።

የዘመን አቆጣጠር ወይም ባህረ ሃሳብ ቁጥር ያለው ዘመን በሚል ትርጉምም ይታወቃል፡፡

ባህረ ሀሳብ እንደ ስያሜው ትንታኔው ጥልቅ መሆኑንና ምስጢሩም የረቀቀ እንደሆነ በዘርፉ ጥናት ያደረጉ ሊቃውንት ይናገራሉ፡፡

በዚህ ውስጥ ደግሞ የኢትዮጵያን የዘመን አቆጣጠር ቀመር ስሌት እናገኛለን፡፡

እንደ መጋቢ ሃዲስ ስቡህ፤ የኢትዮጵያ የዘመን ቀመር ከዩሊዮስም ሆነ ከጎርጎሮሳዊያን አቆጣጠር የተለየ ነው፡፡

“ጎርጎሮሳዊያን የሚከተሉት ከተማቸው ከተመሰረተች በኋላ ከ753 ዘመን ክርስቶስ ተወልዷል ብለው የታሪክን አቆጣጠር ይዘው ስለሄዱ ከኢትዮጵያ ጋር አይገኛኝም” ሲሉ የዘመን አቆጣጠሩ የተለየ መሆኑን አስረድተዋል።