የአሸባሪዎች የጥፋት ተግባር ለማክሸፍ ትግሉ የሚጠይቃውን መስዋዕትነት ሁሉ እንከፍላለን

68

ጎባ፤ ጷጉሜን 03/2013 (ኢዜአ) ከመከላከያ ሰራዊት ጎን በመሰለፍ የአሸባሪዎቹ ህወሃትና ተላላኪው ሸኔን የጥፋት ተግባር ለማክሸፍ ትግሉ የሚጠይቀውን የህይወት መስዋዕትነት ሁሉ እንከፍላለን ሲሉ የባሌ ዞን ወጣቶች አስታወቁ።

ከዞኑ 12 ወረዳዎች የተውጣጡ ወጣቶች በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በባሌ ሮቤ ከተማ በተወያየበት ወቅት እንዳሉት፤ ሀገርን የማስቀጠል ታሪካዊ ግዴታችንን የምንወጣ ወጣቶች እያለን ሀገራችን አትፈርስም፡፡ 

ጀግኖች አባቶቻችን በከፈሉት መስዋዕትነት በነጻነት ያቆዩልንን ሀገር እኛም በተራችን የህይወት መስዋእትነት ጭምር ከፍለን ለተተኪው ትውልድ እናስረክባለን ነው ያሉት።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል የጎባ ወረዳ ነዋሪ ወጣት ጄይላን አማን በሰጠው አስተያየት፤ አሸባሪዎቹ ሸኔና ህወሃት ሀገርን ለማፍረስ የፈጠሩት ጥምረት ድብቅ የሽብር ተግባራቸውን ያጋለጠ መሆኑን ተናግሯል፡፡

ሽብርተኞቹ በንጹሃን ላይ እያደረሱ ያሉት ጥቃት አረመኔያዊና የሚኮነን ተግባር ነው ብሏል፡፡

"የሀገራችንን ህልውና ለማረጋገጥ መንግስት እያደረገ የሚገኘው ዘመቻ በስኬት እንዲጠናቀቅ እስከ ግንባር መዝመት የውዴታ ግዴታ ወድቆብናል" ያለው ደግሞ ከጋሰራ ወረዳ የመጣው ወጣት አብደላ መሐሙድ ነው፡፡

ወጣት አብደላ እንዳለው፤ በመንግስትና ህዝቡ መካከል ልዩነት እንዲፈጠር ያልተገባ የዋጋ ንረት ለመፍጠር እየጣሩ የሚገኙ የሽብርተኞቹ ተላላኪዎች ላይም እርምጃ ሊወሰድ ይገባል፡፡

ወጣቶቹ ከመከላከያ ሰራዊት ጎን በመሰለፍ የአሸባሪዎቹን የጥፋት ተግባር በማክሸፈ ሀገርን ለማዳን ወቅቱ የሚጠይቀውን የህይወት መስዋእትነት ሁሉ እንከፍላለን ሲሉ አስታውቀዋል፡፡

በውይይት መድረኩ የተገኙት የባሌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱልሀኪም አልይ በበኩላቸው፤ የህልውና ዘመቻው እንዲሳካ የዞኑ ማህበረሰብ እያደረገ የሚገኘው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ የሚደነቅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተለይም የነገ ሀገር ተረካቢ ወጣቶች ታሪካዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት አንድ ሆነው በመነሳት ኢትዮጵያን ከሽብርተኞች ጥቃት ለመጠበቅ ያሳዩት ቁርጠኝነት ለሀገራቸው ያላቸውን ፍቅርና ክብር ያሳያል ብለዋል።

በባሌ ዞን የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ለህልውና ዘመቻው ድጋፍ የሚውል ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ ማበርከታቸውንም ዋና አስተዳዳሪው አውስተዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም