አሸባሪው የህወሓት ቡድን ንፁሃን ዜጎችን መንገድ ላይ አሰልፎ ረሽኗል

54

አዲስ አበባ ጳጉሜን 3/2013 (ኢዜአ)አሸባሪው የህወሓት ቡድን ንፁሃን ዜጎችን መንገድ ላይ አሰልፎ መረሸኑን የሰሜን ጎንደር ዞን ዳባት ወረዳ ጭና ቀበሌ ነዋሪዎች ተናገሩ።

ነዋሪዎቹ አሸባሪው ህወሓት በጭና ቀበሌ ንፁሃንን በግፍ መጨፍጨፉን፤ የ6 ወር ህፃን ልጅ በእናቷ ጀርባ እንደታዘለች መግደሉን ተናግረዋል።

ኢዜአ በጭና ቀበሌ ተገኝቶ የዓይን እማኝ የሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎችን አነጋግሯል።

ቡድኑ በሰሜን ጎንደር ዞን ደባት እና ደባርቅ ወረዳን ለመቁረጥ ያደረገው ሙከራ በአገር መከላከያ ሠራዊትና በፀጥታ ሃይሎች ጀግንነት ከሽፎ ሽንፈት ሲደርስበት በአካባቢው ያገኛቸው ንፁሃን ዜጎች ላይ ጭፍጨፋ አድርሶ ሄዷል።

በጅምላ በግፍ የገደላቸው በርካታ ንፁሃን ዜጎች አስከሬንም በጭና ተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያን ተቀብሯል።

ነዋሪዎቹ አሸባሪው የህወሓት ቡድን ነሐሴ 29 ቀን 2013 ዓ.ም በመከላከያ ሠራዊት እና በፀጥታ ሃይሎች ሽንፈት ሲደርስበት በቀበሌው የሚገኙ ንፁሃን ዜጎችን ገድሎ መሸሹን ተናግረዋል።

የዓይን እማኞቹ እንደተናገሩት አሸባሪው ቡድን ንፁሃንን መንገድ ላይ አሰልፎ ነው የረሸናቸው።

ቡድኑ ራሳቸውን መከላከል የማይችሉ አረጋዊያን፣ አካል ጉዳተኞች፣ ህፃናትን እና ታመው ቤት የዋሉ ንፁሃንን መግደሉንም ገልጸዋል።

የ6 ወር ህፃን ልጅ እናቷ ጀርባ ላይ እንደታዘለች መገደሏን፣ የአንድ ቤተሰብ ስድስት አባላትን በግፍ መግደሉንም ነው ነዋሪዎቹ ያረጋገጡት።

ከሟቾቹ መካከል ሁለት የሃይማኖት አባቶች ሚስቶቻቸው እና ልጆቻቸው እንደሚገኙበት የገለጹት ነዋሪዎቹ አሸባሪው ቡድን የቤት እንስሳትን ጭምር እየገደለ መሸሹን አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም