በሶማሌ ክልል ለተከሰተው ሁከትና ረብሻ የክልሉ አመራሮች ኃላፊነቱን መውሰድ አለባቸው--- ሌተናል ጄነራል ሀሰን ኢብራሂም

52
ጂግጂጋ ነሓሴ 7/2010 "በሶማሌ ክልል ባለፈው ሳምንት ጅግጅጋና ሌሎች ከተሞች ለተከሰተው ሁከትና ረብሻ የክልሉ አመራር አካላት ኃላፊነት መውሰድ አለባቸው" ሲሉ ሌተናል ጄነራል ሀሰን ኢብራሂም ተናገሩ፡፡ የክልሉ ሰላምና መረጋጋት ወደ ነበረበት እንዲመለስ የተሰማራው የሀገር መከላከያ ሰራዊት አመራሮች በጅግጅጋ ከተማ ተጎጂዎች፣ ምሁራን፤ የሀገር ሽማግሎች፣ የጎሳ መሪዎች እና ከሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተወያይተዋል፡፡ በአካባቢው በተከሰተው የፀጥታ ችግር መነሻና ቀጣይ የመፍትሄ አቅጣጫ ላይ በጂግጂጋ ከተማ በተካሄደው በዚሁ ውይይት የክልሉ አመራሮችም ተሳትፈዋል፡፡ የውይይት  መድረኩን የመሩት የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር ተወካይ ሌተናል ጄነራል ሀሰን ኢብራሂም እንዳሉት ለስልጣናቸው ሲሉ በክልሉ ለተከሰተው ብጥብጥና ሁከት የክልሉ አመራር አካላት ተጠያቂ ናቸው፡፡ ለስልጣናቸው ሲሉ በፈጠሩት ክፍተት ለጠፋው የሰው ህይወትና ንብረት በወቅቱ የነበሩት የክልሉ አመራሮች ኃላፊነት መውሰድ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል የክልሉ ተወላጅና ምሁር የሆኑ  አቶ ሽኔ የሱፍ በበኩላቸው ስልጣናቸውን ለማስጠበቅ ወጣቱን ለጥፋት በማነሳሳት  ህዝቡን ሰላም እንዲደፈርስ የተንቀሳቀሱ አካላት እንደነበሩ መታዘባቸውን ገልጸዋል፡፡ መንግስት በነዚህ አካላት ላይ ተገቢውን የእርምት እርምጃ  በመውሰድ ተጎጂዎችን መካስ እንዳለበትም አውስተዋል፡፡ የውይይቱ ተሳታፊዎች በሁከቱ የደረሰባቸውን ጉዳት በዝርዝር በማቅረብ ያመላከቱ ሲሆን፤ መሰል ችግር በድጋሜ እንዳይከሰት የድርሻቸውን እንደሚወጡም በሰጡት አስተያየት አረጋግጠዋል፡፡ መንግስት በክልሉ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎችን የሚያሳትፈ ጉባኤ ማዘጋጀት እንዳለበት ተጠቁሟል፡፡ ውይይቱ በተመሳሳይ ጎዴ፣ ደገሀቡር፣ ቀበሪደሃርና በሌሎችም የክልሉ ከተሞች እንደሚቀጥል ታውቋል፡፡ በሶማሌ ክልል ጂግጂጋን ጨምሮ በክልሉ የተለያዩ ከተሞች ተፈጥሮ በነበረው  ሁከት የሰው ህይወትና ንብረት መጥፋቱ ቀደም ብሎ ተገልጿል፡፡        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም