"አርቲስት አለማየሁ እሸቴ ለአገሩ ህያው የሆነ ዘመን ተሻጋሪ የጥበብ ሥራ አበርክቷል"

100

አዲስ አበባ ጳጉሜ 2/2013(ኢዜአ)አርቲስት አለማየሁ እሸቴ ለአገሩ ህያው የሆነ ዘመን ተሻጋሪ የጥበብ ሥራ ማበርከቱን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው ተናገሩ፡፡

የአርቲስቱ የአስክሬን ሽኝት ስነ ስርአት በመስቀል አደባባይ ተከናውኗል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው አርቲስት አለማየሁ እሸቴ ለአገሩ ህያው የሆነ ዘመን ተሻጋሪ የጥበብ ሥራ አበርክቶ አልፏል ብለዋል።

አርቲስት ዓለማየሁን በአካል በማጣታችን ሃዘናችን ጥልቅ ቢሆንም በዘመን ተሻጋሪ ስራዎቹ ሁሌም እናስበዋለን ብለዋል።

ከፈጣሪ የተሰጠውንም ፀጋ ወደ  ሙዚቃ ዓለም ከተቀላቀለበት  ጊዜ አንስቶ ትውልዱን ሲመክር ሲያስተምርበት ቆይቷል ሲሉ ገልፀዋል፡፡

አርቲስቱ  ”ተማር ልጄ” በሚለው ሙዚቃው ኢትዮጵያውያን ለትምህርት እና ስልጣኔ ትኩረት እንድንሰጥ አድርጓል  ብለዋል፡፡

”አዲስ አበባ ቤቴ ” በሚለው ሙዚቃም  ለአገሩ ያለውን ፍቅር  አሳይቶ አልፏል  ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ "አለማየሁ እሸቴ አልሞተም፤ በሥራዎቹ ምክንያት ህያው ሆኖ ይኖራል" ሲሉ ተናግረዋል።

አርቲስት አለማየሁ እሸቴ ከልጅነቱ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ለአገሩ ባበረከተው ሁሉ ታላቅ ባለውለታ መሆኑን ገልጸዋል።

አርቲስት አለማየሁ እሸቴ ነሐሴ 27 ቀን 2013 ዓ.ም ባደረበት የልብ ሕመም በ80 ዓመቱ በድንገት ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱ የሚታወስ ነው።

የአርቲስቱ ስርዓተ ቀብር ዛሬ በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ይፈጸማል።

አርቲስት አለማየሁ እሸቴ የአራት ወንድና የሶስት ሴት ልጆች አባት የነበረ ሲሆን፤ አራት የልጅ ልጆችን ለማየትም በቅቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም