ወደ አገር ለሚገቡ ዳያስፖራዎች የ25 በመቶ የአገልግሎት ክፍያ ቅናሽ እንደሚደረግ ተገለፀ

96
አዲስ አበባ ነሓሴ 7/2010 ወደ አገር ለሚገቡ ዳያስፖራዎች የ25 በመቶ የአገልግሎት ክፍያ ቅናሽ እንደሚደረግ ተገለፀ። የኢትዮጵያ ቱሪዝም ቦርድ ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ወደ ሀገር ለሚመጡ ዳያስፖራዎች ከነሐሴ 9 ቀን 2010 ዓ.ም እስከ መስከረም 20 ቀን 2011 ዓ.ም የሚቆይ የ25 በመቶ የአገልግሎት ቅናሽ ይደረጋል ብለዋል። የቦርዱ ሰብሳቢ አቶ ፍፁም አረጋ እንደገለፁት የአገልግሎት ቅናሹ ወደ አገር የሚመጡ ዳያስፖራዎችን ለማበረታታት ያለመ ነው። አገልግሎትን በቅናሽ ለመስጠት ከወሰኑ ድርጅቶች መካከልም የኢትዮጵያ አየር መንገድ 25 በመቶ የቲኬትና ተዛማጅ አገልግሎት እና የዜግነት ጉዳዮች መምሪያ በሚሰጠው የቪዛ አገልግሎት የ25 በመቶ የክፍያ ቅናሽ እንደሚያደርጉ አቶ ፍፁም ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ አስጎብኚ ማህበር፣ የሆቴሎች ማህበር፣ የታክሲዎች ማህበር እና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶችም በሚሰጡት አገልግሎት ላይ ከጠቅላላ ዋጋ 25 በመቶ ቅናሽና የተለያዩ የማበረታቻ አገልግሎቶች ለመስጠት ቃል መግባታቸውን ተናግረዋል። በነሐሴና መስከረም ወሮች የአሸንዳና አሸንድዬ(ሻደይ) በዓላት፣ የዓረፋ በዓል፣ የቡሄ፣ አዲስ ዓመትና ቅዱስ ዮሃንስ፣ የኢሬቻና የመስቀል በዓሎች እንደሚከበሩ ያስታወሱት አቶ ፍፁም፤ በዚሁ ወቅት ለሚመጡ ዳያስፖራዎች አስፈላጊው አገልግሎት እንዲሰጡ ለአገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች አሳስበዋል። ለሚመጡ ዳያስፖራዎች ፈጣን የሲም ካርድ አገልግሎት ለመስጠትም ኢትዮ-ቴሌኮም ዝግጅት አድርጓል ያሉት አቶ ፍፁም፤ በበዓላትና በአዲስ ዓመት ወቅት የሚታየው የኔትዎርክ መጨናነቅ እንዳይኖርም ከተቋሙ ጋር አብረን እንሰራለን ብለዋል። የኢትዮጵያ ቱር ኦፕሬተር አሶሴሽን ወኪል አቶ ያቆብ መላኩ በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት አሶሴሽኑ በሥሩ ከ200 በላይ የቱር ኦፕሬተሮችን ያቀፈ ሲሆን የ25 በመቶ የአገልግሎት ክፊያ ቅናሽ ያደርጋል። ከዚህ በተጨማሪ ዳያስፖራዎቹ ወደ መጡበት አገር ሲመለሱ አምባሳደር ሆነው አገራቸውን እንዲያስተዋውቁ ለማበረታታት የነፃ አገልግሎት ለመስጠት ጭምር መዘጋጀቱን ነው የተናገሩት። ከሥሩ 118 ባለኮከብ ሆቴሎችን ያቀፈው የአዲስ አበባ የሆቴል ባለቤቶች ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ቢንያም ብስራት በበኩላቸው የ31 ነጥብ 8 በመቶ የመኝታ ክፊያ ቅናሽ ለማድረግና ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት ተዘጋጅተናል ብለዋል። በማህበሩ አባል ያልሆኑት ወደ 40 የሚጠጉ ባለ ኮከብ ሆቴሎችም የቅናሽ አገልግሎቱን የሚሰጡበት ዕድል ለማመቻቸት እንደሚሰሩ አቶ ቢንያም ተናግሯል። በጋዜጣዊ መግለጫው የተገኙ የክልሎች የዘርፉ ተወካዮችም የአገልግሎት ቅናሽ ለማድረግና ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት መደረጉን አረጋግጠዋል። መንግስትም ከዓለም ባንክ ጋር ባደረገው የ1 ሚሊዮን ዶላር የድጋፍ ስምምነት ወንጪ፣ ኤርታአሌ፣ ሻላና አቢያታ፣ የባሌ ተራራዎች፣ የአርባ ምንጭ፣ የሰሜን ተራሮች፣ የገረዓልታ ተራራዎች የመሳሰሉ መዳረሻዎች ላይ አገልግሎትን የማዘመን ሥራዎች እንደሚሰሩ አቶ ፍፁም አረጋ ገልፀዋል። በዚህ የቱሪዝም ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሀብቶችም የአምስት ዓመት የግብር እፎይታ፣ ዕቃዎችን ከቀረጥ ነጻ የማስገባትና መሬትም ከሊዝ ነፃ የሚያገኙበትን ጨምሮ ትላልቅ ማበረታቻዎች የሚደርግባቸው አሰራሮች መዘርጋታቸውን ገልፀዋል። በመላው ዓለም የሚገኙ ዳያስፖራዎች አዲሱን ዓመት መጥተው በእናት አገራቸው እንዲያሳልፉም አቶ ፍፁም ጥሪ አድርገዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም