በነጆ ወረዳ 31 ሺህ ጥይቶችን ሲያዘዋውሩ የተገኙ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

73

ግምቢ/ነገሌ፣ ጷጉሜ 01 ቀን 2013 (ኢዜአ) በምራብ ወለጋ ዞን ነጆ ወረዳ 31 ሺህ ጥይቶችን ሲያዘዋውሩ የተገኙ ሁለት ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ፖሊስ አስታወቀ።

በዞኑ ፖሊስ መምሪያ የአካባቢ ሰላም ማረጋገጥ ምክትል ዳይሬክተር ሳጂን ኦላና ምትኩ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት ነሐሴ 28 ቀን 2013 ዓ.ም ህብረተሰቡ ባደረሰው ጥቆማ መሰረት ነው።

ግለሰቦቹ ሽንኩርት በጫነ ተሽከርካሪ ስር 31 ሺህ የብሬንና የክላንሽኮቭ ጥይቶችን ወደ ቤጊ እያጓጓዙ እያለ ነጆ ከተማ እንዳሉ እንደተደረሰባቸው ገልጸዋል።

በህገ ወጥ መንገድ ጥይቶቹን ሲያዘዋውሩ የተደረሰባቸው ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየተጣራ መሆኑን ገልጸው፤ ወንጀልን ለመከላከል ኅብረተሰቡ እየሰጠ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

ኅብረተሰቡ ከምንጊዜም በላይ ተደራጅቶ ከአሸባሪዎቹ ህወሃትና ሸኔ ተላላኪዎች አካባቢውን በንቃት መጠበቅ እንዳለበትም አመልክተዋል።

በተመሳሳይ ለሽብር ተግባር ሊውል የነበረ ከ2 ሺህ 858 በላይ የክላሽንኮቭና የብሬን ጥይቶች እንዲሁም 36 የጸጥታ አካላት ደንብ ልብስ መቆጣጠሩን የጉጂ ዞን ፖሊስ መምሪያ አስታውቋል፡፡

በመምሪያው የወንጀል መከላከል ምክትል ዳይሬክተር ዋና ሳጂን ጉተማ ሳፌ እንዳሉት፤ ጥይትና የደንብ ልብሱን መቆጣጠር የተቻለው በነገሌ ከተማ አቅራቢያ ቢታታ ቀበሌ  ውስጥ ነው፡፡

ከባሌ ዞን ተነስቶ በጎሮዶላ ወረዳ የገናሌን የውስጥ ለውስጥ መንገድ በማቋረጥ ለሽብርተኛው ሸኔ ለማቀበል የተቃደ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡

በሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3 - 35819 አዲስ አበባ "ኤፍ ኤስ አር" ተሽከርካሪ ላይ እንደተጫነ ዛሬ ከቀኑ አምስት ሰዓት ላይ መቆጣጠር እንደተቻሉ ገልጸው፤ አሽከርካሪው ለጊዜው ቢያመልጥም ለመያዝ ክትትል እየተደረገበት መሆኑን አመልክተዋል።

የጎሮዶላ ወረዳ ህዝብ የሽብርተኛውን ሸኔን የጥፋት ድርጊት አስቀድሞ ለመከላከል ጥቆማ በመስጠት እያደረገ ያለውን ድጋፍ እንዲቀጥልበትም ዋና ሳጂን ጉተማ ጠይቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም