የአሁኑ ትውልድ የኢትዮጵያን ሰላምና ደህንነት በማስጠበቅ ወደ ተሻለ እድገት ማሻገር ይኖርበታል

92

አዲስ አበባ፣ጳጉሜን 1/2013(ኢዜአ)"ኢትዮጵያ በዘመን ቅብብሎሽ ያጋጠሟትን ችግሮች በድል እንዳለፈች ሁሉ የአሁኑ ትውልድም የአገሩን ሕልውና በማስጠበቅ ወደ ተሻለ እድገትና ሰላም ማሻገር ይኖርበታል" ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለጹ።

ጳጉሜን-1 የኢትዮጵያዊነት ቀን "ለኢትዮጵያ ክብር እቆማለሁ፤ እዘምራለሁ" በሚል መሪ ሐሳብ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።

በዝግጅቱ ላይ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት መዓዛ አሸናፊ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የአገር መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ መኮንኖች እና በርካታ የመዲናዋ ነዋሪዎች ታድመዋል።

የጳጉሜን ወር አምስቱም ቀናት “አዲስ አበባ የኢትዮጵያ የድል ነፀብራቅ” በሚል መሪ ሐሳብ በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራሉ።

በኢትዮጵያዊነት የተሰየመው ጳጉሜን-1 ቀንም አገራዊ አንድነትና ኢትዮጵያዊነትን ከፍ በሚያደርጉ ዝግጅቶች በመከበር ላይ ይገኛል።

በዝግጅቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ "ኢትዮጵያዊነታችን ማንነታችንና ክብራችን የጥንካሬ ምንጭ መገለጫችን ነው" ብለዋል።

ኢትዮጵያን "ከፍ ከፍ ለማድረግም ለክብሯ እንቆማለን ለእርሷም እንዘምራለን" ሲሉ ገልጸዋል።

ለኢዜአ ሐሳባቸውን ያጋሩ የመዲናዋ ነዋሪዎች እንዳሉት፤ ኢትዮጵያዊነት በጥንት አባቶች አኩሪ ተጋድሎ የተገነባ ለነገ ትውልድም የሚሻገር መሆን አለበት።

ኢትዮጵያ በዘመን ቅብብሎሽ ያጋጠሟትን ችግሮች በድል እንዳለፈች ሁሉ የአሁኑ ትውልድም የአገሩን ሕልውና በማስጠበቅ ወደ ተሻለ እድገትና ሰላም ማሻገር ይጠበቅበታል ነው ያሉት።

ቄስ በቆየ መሰረት እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያዊነት ማለት በጀግንነት፣ በብሔርና ጎሳ የማይታጠር በመደጋገፍ የታጀበ መልካምነት ነው።

ይህን አስቸጋሪ ጊዜ በድል ለማለፍም ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአንድነትና በተባበረ ክንድ ለቀጣይ ትውልድ ማስረከብ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

እንደ ወይዘሮ ፍሬህይወት መኮንን ገለጻም፤ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በማስጠበቅ ለቀጣይ ትውልድ የተሻለች አገርን ለማስረከብ በማለት ወንድ ልጃቸውን ወደ አገር መከላከያ ሠራዊት በክብር መርቀው መላካቸውን ተናግረዋል።

"አገር ሲኖር ነው መብላትም ይሁን መጠጣት የሰላም አየርም መተንፈስ የሚቻለው" የሚሉት ወይዘሮ ፍሬህይወት፤ "ኢትዮጵያዊያን በጎሳና ኃይማኖት ሳንከፋፈል በአንድነት መቆም ከቻልን ጠላትን በቀላሉ መመከት ይቻላል" ብለዋል።

ወጣት ሳለ-እግዚአብሔር መላኩ በበኩሉ፤ ጥንት አባቶች አኩሪ ገድልና ታሪክ ፈጽመው ያቆዩትን አገር አንድነት በማጽናት ያጋጠሟትን ችግሮች በመመከት "ለቀጣይ ትውልድ የተሻለች ኢትዮጵያን ማውረስ ይገባል" ብሏል።

"ኢትዮጵያ በዘመን ቅብብሎሽ ሲያጋጥሟት የነበሩ ችግሮችን እንዳለፈች ሁሉ የአሁኑ ትውልድም የአገሩን ሰላምና ደህንነት በማስጠበቅ ወደ ተሻለ እድገትና ሰላም ማሻገር ይጠበቅብናል" ያለው ደግሞ ሌላኛው ወጣት ለዓለም ዋሲሁን ነው።

በቀጣዮቹ ቀናት ጳጉሜን-2 የአገልጋይነት ቀን፣ ጳጉሜን-3 የመልካምነት ቀን፣ ጳጉሜን-4 የጀግንነት ቀን፣ ጳጉሜን-5 የድል ቃል-ኪዳን ብሥራት ቀን ሆነው በተለያዩ ዝግጅቶች እንዲከበሩ መርሃ-ግብር ወጥቶላቸዋል።

በነገው እለትም ጳጉሜን-2 ለትራንስፖርት አገልግሎት ተጠቃሚዎች የተቀላጠፈ አገልግሎት በመስጠት የማህበረሰብ አገልጋይነት የሚገለጽበት ቀን እንዲሆን መርሃ-ግብር ተይዞለታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም