የአፍንጮ በር ጤና ጣቢያ ነፍሰጡር እናቶችን በቀዶ ህክምና ማዋለድ እንዳልቻለ አስታወቀ

68
አዲስ አበባ ነሀሴ 7/2010 በአዲስ አበባ ከተማ ጤና ቢሮ የአፍንጮ በር ጤና ጣቢያ ነፍሰጡር እናቶችን በቀዶ ህክምና ማዋለድ እንዳልቻለ አስታወቀ። የጤና ጣቢያው ሜዲካል ዳይሬክተር አቶ አባተ ዳምጠው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በምጥ መውለድ የማይችሉ ነፍሰጡር እናቶችን በቀዶ ህክምና ለማዋለድ ዝግጅት አልተደረገም። በጤና ጠቢያው በቀዶ ህክምና ለማዋለድ ተብሎ የተዘጋጀው ክፍል በአሁኑ ወቅት መድኃኒት ቤት በመሆን እያገለገለ ነው። መድሃኒት ቤቱን ለማዛወርና ክፍሉን ለማስለቀቅ ግንባታ የተጀመረ ቢሆንም መጠናቀቅ አለመቻሉ በቀዶ ህክምና የማዋለድ አገልግሎት ለመጀመር ያላስቻለ መሆኑን አቶ አባተ ተናግረዋል። ጤና ጣቢያው በቀዶ ህክምና ማዋለድ የሚያስፈልጋቸው ነፍሰጡር እናቶችን ወደ ሌሎች ሆስፒታሎች እንደሚልክ የገለጹት ሜዲካል ዳይሬክተሩ ከግንባታ ጋር በተያያዘ የተፈጠረው ችግር ሲፈታ አገልግሎቱ ከየካቲት 12 ሆስፒታል ጋር በትብብር እንደሚሰጥ ጠቁመዋል። በተመሳሳይ የአልትራሳውንድ አገልግሎት ለመጀመር ጤና ጣቢያው ቢያቅድም በክፍል ጥበት ሳቢያ ሊሳካለት አለመቻሉን ገልጸዋል። እንደ አቶ አባተ ገለጻ በጤና ጣቢያው የሚከናወነው ግንባታ መቋረጡን አስመልክቶ ግንባታውን የሚያስተዳድረው የአራዳ ክፍለ ከተማ ኮንስትራክሽን ጽህፈት ቤት በደብዳቤ እንዲያውቀው ተደርጓል። እንዲሁም በከፍተኛ ዝናብ ምክንያት የፈረሰው የጤና ጣቢያው አጥር እንዲገነባ ጥያቄ መቅረቡንም ተናግረዋል። የአራዳ ክፍለ ከተማ የመንግስት ኮንስትራክሽን ዋና የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ተፈራ አሰፋ በበኩላቸው በጤና ጣቢያው የሚገነባው መድኃኒት ቤት ግንባታ 80 በመቶ ደርሶ ተቋራጩ በዋጋ ንረት ሳቢያ ተጨማሪ ክፍያ በመጠየቅ ግንባታውን እንዳቆመው ገልጸዋል። ክፍለ ከተማው ከተቋራጩ ጋር ውይይት አድርጎ ግንባታው ይጀመራል ተብሎ ቢጠበቅም ተቋራጩ ፈቃደኛ ሳይሆን መቅረቱን ተናግረዋል። የግንባታው ባለቤት የክፍለ ከተማው ጤና ጽህፈት ቤት መሆኑን የገለጹት አቶ ተፈራ ከተቋራጩ ጋር ያደረገው ውል ስላልተቋረጠ ግንባታውን ለሌላ ተቋራጭ ለመስጠት መቸገራቸውን ተናግረዋል። በዝናብ የፈረሰውን አጥር ግንባታ ለሚያከናውነው ማህበር ቅድመ ክፍያ ስላልተፈጸመ የቁፋሮ ሥራ ተጀምሮ መቆሙን ገልጸዋል። ከክፍለ ከተማው ጤና ጽህፈት ቤት መሟላት የሚገባቸው ጉዳዮች ከተሟሉ ግንባታው በአጭር ጊዜ እንደሚጠናቀቅ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም