በአገር ውስጥ የመድሃኒት ምርት አቅርቦትን ለማሻሻል እየሰሩ መሆኑን የአገር ውስጥ አምራቾች ገለጹ

413

ነሀሴ 30/2013 ከውጭ የሚገባውን መድኃኒት በአገር ውስጥ ምርት ለመተካት እየሰሩ መሆኑን የአገር ውስጥ አምራቾች ገለጹ።

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ከመድኃኒት አቅራቢዎች እና ሌሎች ባለድርሸ አካላት ጋር በአዲስ አበባ ውይይት አድርጓል።

በውይይቱ ላይ የተገኙት የአገር ውስጥ መድሃኒት አምራቾች በተያዘው ዓመት ከውጭ የሚገባውን መድኃኒት በአገር ውስጥ ምርት ለመተካት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ አሁን ላይ 85 በመቶ የሚሆነው አጠቃላይ የመድኃኒት አቅርቦት ከውጭ የሚገባ መድሃኒት ነው የሚሸፈነው።

አቅርቦቱን በአገር ውስጥ ምርት ለመሸፈን የሚያስችል አቅም ቢኖርም በተለያዩ ምክንያቶች አለመሳካቱን የገለጹት አምራቾቹ ዘንድሮ ለመሸፈን ጥረት እደርጋለን ብለዋል።

የክልች ኢስትሮ ባዮቴክ የመድኃኒት ፋብሪካ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ዳኒሄል ዋቅቶሌ፤ ፋብሪካቸው መምረት ለመጀመር ሁሉንም ቅድመ ዝጅት አጠናቆ ወደ ምርት ሲገባ ወደ አገር የሚገባ ምርትን ያስቀራል ብለዋል።

የአገር ውስጥ ፍጆታን ከመተካት በተጨማሪ ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሬ ለማስገኘትም እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በዘርፉ በርካታ የሰለጠነ የሰው ኃይል ስላለ የአገር ውስጥ ባለሙያዎች ባላቸው እውቀት በአጭር ጊዜ የውጪውን የመተካት አቅም እንዳለቸው ተናግረዋል።

የሸንግ የመድኃኒት ፋብሪካ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ያሬድ ሂርጶ፤ ፋብሪካቸው ከሶሰት ዓመት በፊት ጀምሮ መድሃኒት እያመረተ መሆኑን ጠቁመው አሁን ላይ ከውጭ የሚገቡትን ተመሳሳይ ምርቶች እየተካ መሆኑን ገልጸዋል።

ክልች ኢስትሮ ባዮቴክ የመድኃኒት ፋብሪካ ምከትል ስራ አስኪያጅና አቶ ዳኒሄል ዋቅቶሌ

አቶ ያሬድ ሂርጶ  የሸንግ የመድኃኒት ፋብሪካ ምክትል ስራ አስኪያጅ  በበኩላቸው

የአገር ውስጥ አምራቾቹ በሙሉ አቅማቸው ወደ ምርት እንዳይገቡ ከውጭ ጥሬ እቃ ሲገባ በማጓጓዝና በውጭ ምንዛሬ ችግር እንዳለ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ባህርና ትራንስፖርት ሎጂስቲክስ ድርጅት ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ ሲራጅ አብዱላሂ፤

በማጓጓዝም በሆነ በወደቦች ከየትኛውም እቃ በላይ ቅድሚያ ለመድኃኒት እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

የኤጀንሲው ጨረታ አስተዳደር ጊዜያዊ ዳይሬክተር አቶ ጥበቡ ሃይሉ፤ ሰነዶች ጋር ተያይዞ የግዥ መዘግየት እንዳይከሰት ኢሌትሮኒክስ ግዢ በዚህ ዓመት ይተገበራል ብለዋል።

በፓይለት ደረጃ በ9 ተቋማት ባለፈው ዓመት የተጀመረው የኢሌትሮኒክስ ግዥ በዚህ ዓመት በስፋት ስራ ላይ ይውላል ብለዋል።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ፤ በመድሃኒት አቅርቦት ላይ የሚስተዋለውን ችግር ለመፍታት የሁሉም ባለደርሻ አካላት ጥረት ያስፈልጋል ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በመድሃኒት አቅርቦት ላይ የሚስተዋለውን ችግር ለመፍታት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ጥረት ያስፈልጋል ብለዋል።

የአገር ውስጥ አቅም መገንባት ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም ኮቪድ 19 በተከሰበት ወቅት አስተምሮናል ሲሉም ጠቁመዋል።

የአገር ውስጥ የመድሃኒት ምረት አቅርቦት ችግርን ለማቃለል በጋራ መስራት እንደሚገባ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ አለምጸሐይ ጳውሎስ ገልጸዋል።

የመድሃኒት አቅርቦትን ለማሳደግ በልዩ ትኩረት የሚሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

መንግስት የዜጎችን የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው ለዘርፉ ስኬት የመድሃኒት አቅርቦት መሟላት ወሳኝ መሆኑንም አንስተዋል።

በመሆኑም በቀጣይ የአገር ውስጥ ምርት የመድሃኒት አቅርቦትን ለማሳደግ በልዩ ትኩረት መስራትን ይጠይቃል ነው ያሉት።