አሸባሪው ህወሓት በገባባቸው ግንባሮች ሁሉ የሰራዊቱን ምት መቋቋም ባለመቻሉ በሽሽት ላይ ነው

340

ነሐሴ 30 ቀን 2013 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሓት በገባባቸው ሁሉ የመከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ልዩ ሃይልና ሚሊሻን ምት መቋቋም ባለመቻሉ በሽሽት ላይ መሆኑን በወሎ ግንባር ከፍተኛ ወታደራዊ አመራር ገለጹ።

የግንባሩ ከፍተኛ ወታደራዊ አመራር እንዳሉት፤ አሸባሪው የህወሃት ቡድን በተለያዩ አቅጣጫዎች ሰርጎ በመግባት የተለያዩ የጥቃት ሙከራዎችን አድርጎ ክፉኛ ተመትቷል።

በመከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ልዩ ሃይልና ሚሊሻን እንዲሁም በየአካባቢው ማህበረሰብ የሚደርስበትን ጠንካራ ምት መቋቋም ባለመቻሉ በፍጥነት ወደ ኋላ በመሸሽ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

“በመሆኑም የሽብር ቡድኑ በተበታተነባቸው አካባቢዎች ሁሉ የህዝቡና የፀጥታ ሃይሉ ቅንጅት ተጠናክሮ የሚቀጥል በመሆኑ እየተሳደደ ይደመሰሳል” ብለዋል።

የሽብር ቡድኑ ይዞት የመጣውን የሰው ሃይልና ሎጂስቲክስ እያጣ መሆኑን ገልጸዋል።

“የህዝቡ ደጀንነትና ተዋጊነት ለሰራዊቱ የላቀ የሞራል ስንቅ በመሆኑ የአሸባሪውን አከርካሪ መስበር ተችሏል” ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት አሸባሪ ቡድኑ በሁሉም አቅጣጫዎች ተበታትኖ ሽሽት ላይ የሚገኝ መሆኑንም ተናግረዋል።