ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የጅማ ኢንዱስትሪ ፓርክን ጎበኙ

119
ጅማ ነሀሴ 7/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ግንባታው በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘውን የጅማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶች ከመጡ ባለሀብቶች ጋር በመሆን ጎበኙ። የጅማ ከተማ ከንቲባ አቶ መክዩ መሃመድ እንደገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፓርኩ በተጨማሪ በጎማና በጌራ ወረዳ በመገኘት የአካባቢውን የተፈጥሮ ቡና ማሳዎችና ለግብርና ያለውን አመቺነት ጎብኝተዋል። በጉብኝቱ ላይ የተካፈሉት ባለሃብቶችም በኢንዱስትሪ ፓርኩና በዞኑ በሚገኙ ወረዳዎች በግብርና ስራ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳሳዩ ተናግረዋል። የጅማ እንዱስትሪ ፓርክ በአሁኑ ወቅት በመጀመሪያው የግንባታ ምዕራፍ ዘጠኝ ሼዶችና አስፈላጊ የሆኑ መሰረተ ልማቶች ተሟልተውለት ከ93 በመቶ በላይ የአፈጻጸም ደረጃ ላይ መድረሱን ገልጸዋል። የእንዱስትሪ ፓርኩ ሲጠናቀቅ እንደ ቡና ፣ ማር ፣ ቅመማ ቅመም እና መሰል የግብርና ምርቶችን በማቀነባበር ያለቀለት ምርት ወደ ውጭ በመላክ የአገራችንን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ከንቲባው ተናግረዋል፡፡ "ፓርኩ ለአካባቢው ወጣቶች የስራ እድል በመፈጠር ለከተማው እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያድረግ ሲሆን ዛሬ የተደረገው ጉብኝትም ጅማ ጥንት ወደ ምትታወቅብት የንግድ እንቅስቃሴ ለመመለስ መሰረት ይሆናል" ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም