‘ከምንም በላይ ኢትዮጵያ ትቀድማለች’ በማለት ከአንድ ቤት ወደ ወታደራዊ ማሰልጠኛ የገቡ ወንድማማቾች

84

ነሃሴ 30 ቀን 2013 (ኢዜአ) ‘ከምንም በላይ ኢትዮጵያ ትቀድማለች’ በማለት ከተለያዩ ክልሎች ወንድማማቾች በብር ሸለቆ ወታደራዊ ማሰልጠኛ በስልጠና ላይ ይገኛሉ።

ኢዜአ ካነጋገራቸው መካከል በአርሲ ጢጆ ተወልደው አዲስ አበባ ይኖሩ የነበሩት ወንድማማቾቹ ምልምል ወታደር ደመላሽ መለሰ እና  አብረሃም መለሰ ይገኙበታል።

ሁለቱ ወንድማማቾች ወታደር አጎት እንደነበራቸው አስታውሰው፤ ሁል ጊዜ እሱን ሲያዩ ሰራዊቱን ለመቀላቀል ልባቸው ይነሳሳ እንደነበር ገልጸዋል።

''እኛ እያለን አገራችን አትፈርስም'' የሚለው ምልምል ወታደር ደመላሽ ኢትዮጵያን ለመጠበቅ እድሉን በማግኘቱ መደሰቱን ተናግሯል።

ታናሽ ወንድሙ ምልምል ወታደር አብረሃም፤ “ኢትዮጵያ ክብሯ ተጠብቆ እንድትዘልቅ የአሁኑ ትውልድ አባላት ትልቅ አደራ አለብን” ብሏል።

''የእኛ ፍላጎት ከምንም በላይ የኢትዮጵያ ህልውና እና ሉዓላዊነት እንዲጠበቅ ነው፤ ለዚህም ዝግጁ ነን'' ብሏል።

በብርሸለቆ ወታደራዊ ስልጠና እየወሰዱ የሚገኙት ደቡብ ክልል ውስጥ በጌዲዮ ዞን ገደብ ወረዳ የተወለዱት ሶስት ወንድማማቾች አገርን ለመጠበቅ ቁርጠኝነታቸውን ገልጸዋል።

ወንድማማቾቹ ምልምል ወታደር ሳሙኤል ከበደ፣ ዳዊት ከበደና ታሪኩ ከበደ "የጀግኖች መፍለቂያ የሆነችውን አገራችንን ከየትኛውም ሃይል ለመጠበቅ ዝግጁ ነን" ብለዋል።

በማሰልጠኛ ትምህርት ቤቱ ከአንድ ቤተሰብ የወጡ አራት ወንድማማቾችም በስልጠና ላይ ይገኛሉ።

የምዕራብ አርሲ ነጌሌ አርሲ ተወላጆቹ የአቶ ኑሪ አራት ልጆች በብር ሸለቆ መሰረታዊ ወታደራዊ ስልጠና እየወሰዱ ይገኛሉ።

ምልምል ወታደር ቃሲም ኑሪ፤ ታጁ ኑሪ፣ በዳሶ ኑሪ እና ዘይኑ ኑሪ ከስልጠና በኋላ የአገራቸው ዘብ ለመሆን መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

''ጤነኛ ሆነን ሳለን ኢትዮጵያ እየተደፈረች፣ እየደማች ለምን እንቀመጣለን ብለን ነው አገራችንን ለመጠበቅ የመጣነው" ይላሉ አራቱ ወንድማማቾች።

ወንድማማቾቹ ሰራዊቱን ለመቀላቀል ለቤተሰባቸው ካሳወቁ በኋላ በቤተሰብና በአካባቢ ሽማግሌዎች ምርቃት እንደተሸኙ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም