ሰርጎ የገባውን ቡድን ባለበት ለመደምሰስ ቆርጠን ተነስተናል

295

ደሴ፣ ነሃሴ 30 ቀን 2013 (ኢዜአ) ”ሰርጎ የገባውን አሸባሪውን ህወሃት ባለበት ለመደምሰስ ቆርጠን ተነስተናል” ሲሉ ግንባር የዘመቱ የደሴ፣ ኮምቦልቻና ሀርቡ ከተማ ወጣቶች ገለጹ።

የደቡብ ወሎ ዞን ወጣቶች ወረባቦና ተሁለደሬ ወረዳዎች ሰርጎ የገባውን አሸባሪ ቡድን ከአገር መከላከያ ሰራዊቱና ከሌሎች የጸጥታ ሃይሎች ጎን ተሰልፈው ለመቅብር በግንባር ፊት ለፊት መፋለም ጀምረዋል፡፡

የደሴ፣ ኮምቦልቻና የሀርቡ ከተማ ነዋሪዎች፣ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት በወረባቦና ተሁለደሬ ግንባር ተገኝተው ወጣቶችንና ሰራዊቱን አበረታተዋል፡፡

የደሴ ከተማ ነዋሪ ወጣት ይማሙ አህመድ ለኢዜአ እንደገለጸው፤ አሸባሪው የህወሃት ቡድን የጀመረውን ወረራና ሀገር የማፍረስ ሴራ በተባበረ ክንድ ማክሸፍ ያስፈልጋል፡፡

በአማራና አፋር ክልሎች በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች ህዝብ እያሰቃየ የሚገኘውን አሸባሪ ቡድን ለመደምሰስ አገራዊ ግዴታውን ለመወጣት መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ለመከላከያ፣ ልዩ ኃይሉና ለፀጥታ አባላት ትጥቅና ስንቅ በማቀረብ ደጀን ከመሆን ባለፈ  እስከ ህይወት መስዋዕትነት ለመክፈል በወረባቦ ግንባር እየተፋለመ መሆኑን ተናግሯል፡፡

“አሸባሪውን ቡድን ሳንቀብር ወደ ደሴ ላንመለስ ከጓደኞቻችን ጋር ተማምለን ዘምተናል” ያለው ወጣቱ፤  ሁሉም ቡድኑን ባለበት ቦታ ሄዶ መቅበር እንጅ ከቤቱ እስኪመጣ መጠበቅ እንደሌለበት ገልጿል፡፡

የኮምቦልቻ ከተማ ነዋሪ ወጣት ሰይድ መሃመድ በበኩሉ “ህብረተሰቡ በአሉባልታ ወሬ ከመረበሽና አካባቢውን ለቆ ከመወጣት ይልቅ ቡድኑን ባለበት ፊት ለፊት መፋለምና የጀግንነት ታሪክ መስራት ይገባል” ብሏል።

አሸባሪው ህወሀት የሰራዉ ግፍ አልበቃው ብሎ ሀገር ለማፍረስ የጀመረውን ግድያ፣ ወረራና ዘረፋ ለመጨረሻ ጊዜ ለማስቆም ግንባር መገኘቱን ገልጿል።

”ወሎ የአሸባሪው ህወሓት መቀበሪያ እንጅ መፈንጫ ባለመሆኑ ሰርጎ በገባበት ቦታ ለመቅበር ወደ ግንባር ዘምተን ሀገራዊ ግዴታችንን በተግባር እየተወጣን ነው” ያለው ደግሞ የሀርቡ ከተማ ነዋሪ ወጣት ታጠቅ አብርሃ ነው፡፡

“ቡድኑን በተባበረ ክንድ ለመጨረሻ ጊዜ ቀብረን ህዝብና አገራችንን ነጻ እናወጣለን” ያለው ወጣቱ፤ ቡድኑ ዳግም እንዳይሆን ወስነው መፈናፈኛ በማሳጣት እየመከቱት እንደሆነ ተናግሯል።

የደሴ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አበበ ገብረ መስቀል በበኩላቸው ወጣቱ በተደራጀ አግባብ ግንባር ዘምቶ ደጀንነቱን በተግባር እያሳየ መሆኑን ተናግረዋል።

“ቡድኑ በህዝብ ላይ የሚፈጽመውን ግፍ ለመጨረሻ ጊዜ ለማስቆም ከቤታችን ተቀምጠን እስኪመጣ መጠበቅ የለብንም” ያሉት ከንቲባው ወሎ የቡድኑ መቀበሪያ እንደሚሆን አመልክተዋል።

የተሁለደሬ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ዘውዱ አለልኝ በበኩላቸው በወረዳው ሰርጎ የገባው ቡድን ዳግም እንዳይነሳ ሆኖ እየተቀጠቀጠ በመሆኑ ህብረተሰቡ ሳይደናገጥ በተደራጀ አግባብ አካባቢውን መጠበቅ እንደሚገባው አስገንዝበዋል።