ኢትዮጵያ እንቅርት የሆነባትን አሸባሪ ቡድን በጥበብ የሚያስወግዱላት ጀግኖች ማፍራቷን ቀጥላለች- ዶክተር አብይ አህመድ

636

ድሬዳዋ ፤ ነሐሴ 29/2013(ኢዜአ) ኢትዮጵያ እንቅርት የሆነባትን ማፍያና አሸባሪ ቡድን በጥበብና በአንድነት የሚያስወግዱላት ጀግኖች እያፈራች መቀጠሏን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሀመድ ተናገሩ፡፡

በሰላም ማስከበር ማዕከል የሁርሶ የኮንቲጀንት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ያሰለጠናቸውን መሠረታዊ ወታደሮች ባስመረቁበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት መልዕክት ሀገራችን ኢትዮጵያ በርካታ ስመጥር ጀግኖች አባቶቻችን በደማቸውና አጥንታቸው አጽንተው ያሻገሯት ብቸኛ ነጻ ሀገር መሆኗን አውስተዋል።

የዛሬዎቹ ተመራቂ ወጣት ወታደሮች የአባቶቻችን ጀግንነት በውስጣቸው አስርጸው ኢትዮጵያ የገጠማትን ነቀርሳና ማፍያ የህውሃት አሸባሪ ቡድን አስወግደው ከነክብሯና ነጻነቷ ለትውልድ ለማሻገር መወሰናቸው የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ታላቅ ክብርና ምስጋና ያቀርባሉ ብለዋል፡፡

በነዚህ ትንታግ ወጣቶች ውስጥ የሚንቦገቦገው የሀገር ፍቅርና ክብር የኢትዮጵያ ነጻነት ለዘላለም ፀንቶ እንደሚኖር ነው የገለጹት፡፡

” ማህፀነ-ለምለሟ ኢትዮጵያ አንድነቷን፣ ነጻነቷንና ሉአላዊነቷን ከነሙሉ ክብሯ የሚያስጠብቁላት ትንታግ ፣ደመ-ሞቃቶች መብረቅ የሆኑ ወጣት ልጆች ማፍራቷን ቀጥላለች ” ብለዋል፡፡

የሀገር ፍቅርና ክብርን የተከናነቡት ጀግኖች ልጆቿ ኢትዮጵያን ለማሸበርና ለማፍረስ የተነሳውን አሸባሪው የህውሃት ቡድን ላይ እየፈፀሙ የሚገኙት ገድል የዚህ ማሳያ ይሆናል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

የህወሃት ቡድን አሸባሪ ሆኖ ተፈጥሮ አሸባሪ ሆኖ አስተዳድሮና አሸባሪ ሆኖ ከስልጣን የተወገደ ቡድን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህን የሀገር እንቅርትና ማፍያ ቡድን በማጥፋት የተሻለችና የበለጸገች ሀገር ለትውልድ ለማስተላለፍ አሁንም ጥበብና ብልሃት የተሞላበት አንድነትና ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

የህወሃት የሽብር ተግባር ከጫፍ ጫፍና በመላው አለም የሚገኙ ትውልዶችን ልክ እንደ አድዋው ዘመን በአንድነት ያፀናና ኢትዮጵያን ለማሻገር በአንድነት የመትመምን ጽናት ፈጥሯል ብለዋል፡፡

ይህ ደግሞ በተሻለ ብልሃትና በፀና አንድነት የበለጸገችና የተሻለች ሀገር ለትውልድ የማስረከቡን ጉዞ የሰመረ እንደሚያደርገው አስታውቀዋል፡፡

የሀገር መከላከያ ሠራዊት ኢታማዦር ሹም ጀነራል ብርሃኑ ጁላ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ሠራዊት በጥብቅ ወታደራዊ ዲሲፒሊን ታንጾ በቀሰመው ዘመናዊ ዕውቀት አሸባሪውን ህወሃት ድባቅ በመምታት አኩሪ ድል በማስመዝገብ ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የዛሬ ተመራቂ ወጣት ወታደሮች የዚህ ጀግና ሠራዊት አካል በመሆናቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡

የሀገር መከላከያ ሠራዊት እያስመዘገበ ለሚገኘው ድል የመላው ህዝብ አንድነታዊ ደጀንነት፣ የማሰልጠኛ ትምህርት ቤቶች መምህራንና አሰልጣኞች ትጋት አስተዋጽኦው የጎላ መሆኑን ነው ጀነራል ብርሃኑ ጁላ ያስታወቁት፡፡

የሁርሶ ኮንቲጀንት ማስልጠኛ ትምህርት ቤት አዛዥ ኮሎኔል አዲሱ ተርፋሳ ፤ የሶስተኛ ዙር ተመራቂ የሠራዊቱ አባላት በቀሰሙት ሁለንተናዊ ጥበብና እውቀት በመታገዝ ከሠራዊቱ ጎን በመሰለፍ ኃላፊነታቸውን በቁርጠኝነት እንደሚወጡ እምነታቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በምረቃው ስነ-ስርዓት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጨምሮ ሚኒስትሮችና የሀገሪቱ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች ተገኝተዋል፡፡