የድምፃዊ አለማየሁ እሸቴ ሥርዓተ ቀብር የፊታችን ማክሰኞ ይፈጸማል

125

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 29/2013(ኢዜአ) የድምፃዊ አለማየሁ እሸቴ ሥርዓተ ቀብር የፊታችን ማክሰኞ ጳጉሜን 2 ቀን 2013 በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል እንደሚፈጸም የአርቲስቱ የቀብር አስፈጻሚ ኮሚቴ አስታወቀ።

የአርቲስቱ የአስክሬን ሽኝት በመስቀል አደባባይ እንደሚከናወንም ተገልጿል።

አርቲስት አለማየሁ እሸቴ ከትናንት በስቲያ ነሐሴ 27 ቀን 2013 ባደረበት የልብ ሕመም በ80 ዓመቱ በድንገት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።

የኮሚቴው አባል የሙዚቃ ባለሙያ ዳዊት ይፍሩ የአርቲስቱን የቀብር ሥነ ሥርዓት እንዲያስተባብር የተቋቋመው ኮሚቴ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት፣ ከአዲስ አበባ ከንቲባ ጽህፈት ቤትና ከኢትዮጵያ የሙዚቃ ዘርፎች ማኅበራት ሕብረት መዋቀሩን ገልጿል።

የአርቲስት አለማየሁ እሸቴ የቀብር ስነ ሥርዓት ጳጉሜን 2 ቀን 2013 ዓ.ም በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል እንደሚፈጸምና ከሥርዓተ ቀብሩ በፊት በመስቀል አደባባይ ሽኝት እንደሚካሄድ መርሃ ግብር ከረፋዱ 5 ሠዓት እስከ ቀኑ ዘጠኝ ሠዓት ድረስ እንደሚቆይ አስታውቋል።

አርቲስት አለማየሁ እሸቴ በ1933 ዓ.ም በአዲስ አበባ አራት ኪሎ ተስፋ ገብረ ስላሴ ማተሚያ ቤት አካባቢ ነው የተወለደው።

ወርቃማው የኢትዮጵያ ሙዚቃ ዘመን ተብሎ በሚጠራው ዘመን ገናና መሆን ከቻሉት ዕንቁ ኢትዮጵያዊ ድምጻዊያን መካከል አንዱ የሆነውን አለማየሁን ወላጅ እናቱ ወይዘሮ በላይነሽ ዮሴፍ በሁለት ወር ዕድሜው ወደ ደሴ ይዘውት ሄደው እስከ ሶስት ዓመቱ በዚያው አድጓል።

በወቅቱ የከተማ ታክሲዎች ያሽከረክሩ ከነበሩ ጥቂት ሰዎች መካከል አንዱ የሆኑት ወላጅ አባቱ አቶ እሸቴ አንዳርጌ ትምህርት ይማር ብለው ወደ አዲስ አበባ አምጥተውት የአብነት ትምህርት አስተምረውታል።

በመቀጠልም ታዳጊው ዓለማየሁ በሊሴ ገብረማርያም፣ በዑመር ሰመተር፣ በአብዮት ቅርስ እና በአርበኞች ትምህርት ቤቶች ትምህርቱን ተከታትሏል፡፡

በአንጋፋ አርቲስቶች መዝገበ ሕይወት የሰፈረው ታሪኩ እንደሚያመለክተው ድምጻዊ አለማየሁ እሸቴ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በአርበኞች ትምህርት ቤት እየተከታተለ ባለበት ወቅት ባደረበት ጥልቅ የሙዚቃ ፍቅር ነበር ፖሊስ ኦኬስትራን የተቀላቀለው። 

ለመጀመሪያ ጊዜ በ1955 ዓ.ም በፖሊስ ሠራዊት ኦኬስትራ ውስጥ በመቀጠር የሙዚቃ 'ሀሁ'ን የጀመረው አንጋፋው ሙዚቀኛ በወቅቱ በሚጫወታቸው የሙዚቃ ስራዎቹ ኤልቪስ ፕሪስሊ የሚል ቅፅል ተሰጥቶትም ነበር።

ከ300 በላይ የሙዚቃ ሥራዎችን ያበረከተው ዓለማየሁ እሸቴ "ጌሪ ኮፐር"፣ "ኢትዮጵያዊው ኤልቪስ"፣ "አለማየሁ ቴክሱ፣ ነጭ ነው ፈረሱ" እየተባለም በአድናቂዎቹ ተወድሷል።

አለማየሁ እሸቴ የኢትዮጵያን ሙዚቃ በዓለም አቀፍ መድረኮች በማቅረብ ተወዳጅነት እንዲያገኝ ያደረገ አንጋፋ ድምጻዊ ነበር።

"ተማር ልጄ" እና "አዲስ አበባ ቤቴ" በሚሰኙት የሙዚቃ ስራዎቹ ተወዳጅነትን ያተረፈው አንጋፋው ሙዚቀኛ የኢትዮጵያን ዘመናዊ ሙዚቃ ከፍ ወዳለ ደረጃ ካደረሱት ድምፃዊያን አንዱ ነው። 

"የወይን ሃረጊቱ"፣ "የሰው ቤት የሰው ነው"፣ "ደንየው ደነባ"፣ "ትማርኪያለሽ"፣ "ወልደሽ ተኪ እናቴ" ከመጀመሪያ ዘፈኖቹ መይጠቀሳሉ።

"እዬዬ"፣ "ማሪኝ ብዬሻለሁ" በተሰኙ ዜማዎቹና "ስቀሽ አታስቂኝ"፣ "ማን ይሆን ትልቅ ሰው"፣ "እንደ አሞራ ክንፍ አውጥቼ ልብረራ" በሚሉት ዘፈኖቹም በብዙዎቹ ዘንድ የሚታወስ አርቲስት ነው።

ለባለቤቱና ለልጆቹ እናት ማቆላመጫ "ውዷ ባለቤቴ" የምትል ዜማ ተጫውቷል። አርቲስቱ በርካታ ዜማዎቹን በሸክላ አስቀርጾ ለገበያም አውሏል። 

በኢትዮጵያ የግል ሸክላ ሙዚቃ ህትመት ታሪክም በአምሃ ሬከርድስ አማካኝነት ያሳተመ የዘመናዊ ሙዚቃ ባለሙያ ነበር።

አርቲስት አለማየሁ እሸቴ "ጤዛ" በተሰኘው የፕሮፌሰር ሐይሌ ገሪማ ፊልም ላይም በሙያው ተሳትፏል።

ከትናንት በስቲያ ነሐሴ 27 ቀን 2013 ሕይወቱ ያለፈው አርቲስት አለማየሁ እሸቴ ከአገር ውስጥና ከዓለም አቀፍ ተቋማት በሙዚቃ ስራዎቹ በርካታ ሽልማቶችን አግኝቷል።

አርቲስት አለማየሁ እሸቴ የአራት ወንድና ሶሰት ሴት ልጆች አባት ሲሆን አራት የልጅ ልጆችንም ለማየት በቅቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም