ከትርፍ ይልቅ አገርና ሕዝብን ያስቀደሙ የግል ትምህርት ቤቶችን ማመስገን ያሻል

87

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 29/2013(ኢዜአ) ለመጪው የ2014 የትምህርት ዘመን ወርሃዊ ክፍያ ጭማሪ ባለማድረግ ከትርፍ ይልቅ አገርና ሕዝብን ያስቀደሙ የግል ትምህርት ቤቶች ሊመሰገኑ ይገባል።

ኢትዮጵያ በአሸባሪው የህወሓት ቡድንና ተመሳሳይ አጀንዳ ይዘው በሚንቀሳቀሱ አካላት የተደቀነባትን አደጋ ለመመከት ዜጎቿ "ኢትዮጵያን ለማዳን እዘምታለሁ፤ መቼም፣ የትም፣ በምንም" ብለው በአንድነት የቆሙበት ወቅት ነው።

አገር ለማዳን ሁሉም ወደ ግንባር ባይዘምትም በየተሰማራበት የስራ መስክ በመተሳሰብ፣ በመተባበርና እጅ ለእጅ በመያያዝ የተደቀነውን ችግር በጋራ ማለፍ የሚጠይቅም ነው ወቅቱ።

በጦር ግንባር አገር ለማዳን እየተፋለመ ላለው ሠራዊት ደጀን መሆን እንጂ ነጋዴና አገልግሎት ሰጪውን ጨምሮ አንዱ በሌላው ላይ የሚያተርፍበት ሳይሆን ከመቼውም ጊዜ በላይ እርስ በእርስ የሚደጋገፉበት ነው።

ኢዜአ "ኢትዮጵያን ለማዳን እዘምታለሁ፤ መቼም፣ የትም፣ በምንም" ሲሉ የገቡትን ቃል የጠበቁ በአዲስ አበባ የሚገኙ ከ700 በላይ የግል ትምህርት ቤቶች አገር ያለችበትን ፈታኝ ወቅት ከግምት በማስገባትና የወላጆችን ጫና ለመቀነስ በ2014 የትምህርት ዘመን የክፍያ ጭማሪ አለማድረጋቸውን ተመልክቷል።

በመዲናዋ ከ1 ሺህ 700 በላይ የግል ትምህርት ቤቶች እንደሚገኙና ከእነዚህ መካከል 700ዎቹ ለአዲሱ የትምህርት ዘመን የክፍያ ጭማሪ አለማድረጋቸውንም ከአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ አረጋግጧል።

የክፍያ ጭማሪ ካላደረጉት ትምህርት ቤቶች መካከል የማቪዝ አጸደ ህጻናትና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር አቶ በቀለ ቶሌራ አገር ያለችበት ሁኔታ ትርፍ የሚታሰብበት አለመሆኑን ነው የገለጹት።

በጦርነቱ ምክንያት በምጣኔ ሃብቱ ላይ የደረሰውን ጫና ታሳቢ በማድረግ ከትርፍ ይልቅ አገርና ሕዝብን በማስቀደም በ2014 የትምህርት ዘመን የክፍያ ጭማሪ ላለማድረግ መወሰናቸውን ተናግረዋል።

አገር የተደቀነባትን የሉዓላዊነት ፈተና ለማለፍ ለአገሩ ሁሉም ጦር ግንባር ባይዘምትም በተሰማራበት የስራ ዘርፍ ለኅብረተሰቡ ወቅቱን ያገናዘበ አገልግሎት መስጠት ተገቢ ነው ብለዋል።

ልጆቻቸውን በትምህርት ቤቱ የሚያስተምሩ ወላጆችም ትምህርት ቤቱ አገር ያለችበትን ፈታኝ ወቅትና የኑሮ ውድነት ከግምት በማስገባት የክፍያ ጭማሪ ባለማድረጉ አመስግነዋል።

የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ አቶ ዘላለም ሙላቱም "አሁን ያለንበት ነባራዊ ሁኔታ በመተሳሰብና በመደጋገፍ የምንሻገረው እንጂ አንዱ በአንዱ ላይ ተንጠላጥሎ የሚያልፍበት አይደለም" ብለዋል።

በከተማዋ ከሚገኙ ከ1 ሺህ 700 በላይ የግል ትምህርት ቤቶች መካከል 700ዎቹ ለ2014 የትምህርት ዘመን ጭማሪ አለማድረጋቸውን በመግለጽ ምስጋና አቅርበዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በኑሮ ውድነት ሳቢያ ኅብረተሰቡ ላይ የሚደርሰውን ጫና ለመቀነስ ለ90 ቀናት የቤት ኪራይ ዋጋ መጨመር የሚከለክል መመሪያ ከቀናት በፊት ማውጣቱ ይታወቃል።

በተመሳሳይም ስንዴ፣ የምግብ ዘይት፣ ስኳርና ሩዝ ከውጭ ሲገቡም ሆነ በአገር ውስጥ ገበያ ላይ ሲውሉ ከማንኛውም ቀረጥና ታክስ ነጻ እንዲሆኑ መወሰኑን የገንዘብ ሚኒስቴር ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም