ሀገር አፍራሹ አሸባሪው ህወሃት የፈፀመው ጥፋትና ሽብር ኢትዮጵያውያን በፀና አንድነትና መንፈስ እንዲተሙ አድርጓል-ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ

90

ነሐሴ 29/2013 (ኢዜአ)ሀገር አፍራሹ አሸባሪው ህወሃት የፈፀመው ጥፋትና ሽብር የኢትዮጵያን ዜጎች ከጫፍ ጫፍ በፀና አንድነትና መንፈስ እንዲተሙ አድርጓል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ ይህን ያሉት የሁርሶ የኮንቲጀንት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት በመሠረታዊ ወታደርነት ሙያ ያሰለጠናቸውን ምልምል አባላት ምረቃ ስነ-ስርዓት ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት ነው።

በእናንተ ውስጥ የሚንተገተገው ፅናትና ቁርጠኝነት ኢትዮጵያን ያሻግራል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያን ሉአላዊነቷንና ነጻነቷን የሚያስከብር ጀግና ማፍራት ማህጸኗ አያቋርጥም ብለዋል።

ይህ ባለፉት ሶስት አስርት ዓመታት ያልታየ አንድነትና ህብረት ሀገር ለማዳን እየዋለ እንዳለ ሁሉ ኢትዮጵያን ወደ ብልፅግና እና ልማት ማሻገር እንዳለበትም አሳስበዋል።

ለተመራቂ ወታደሮች ኢትዮጵያን ለማፅናትና ለማሻገር ወደዚህ የተከበረው የወታደር ሙያ በመቀላቀላቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ተመራቂ ወታደሮች በተሰማሩበት ስፍራ ድልና ጀብድ ፈፅመው እንደሚመለሱ ዕምነታቸው የፀና መሆኑንም ገልጸዋል።

“ሀገርን ለማዳን ከጫፍ ጫፍ የሚደረገው ርብርብ በስኬት ተጠናቆ የታፈረችና የተከበረች ኢትዮጵያ ለትውልድ መሸጋገሯ የፀና ዕውነት ነው” ብለዋል።

በምረቃው ስነስርዓት ላይ የተገኙት የሀገር መከላከያ ሠራዊት ኢታማዦር ሹም ጀነራል ብርሃኑ ጁላ እንደተናገሩት፤የአገር መከላከያ ሠራዊት ከግዳጅ ያለመታከት በፀና ጀግንነት ጀብድ እየፈፀመ የሚገኝ ቆራጥ ሠራዊት ነው ብለዋል።

ሠራዊቱ አሸባሪው ህወሃት ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚፈፅመውን ሴራ እየበጣጠሰ መሆኑንም ተናግረዋል።

አሸባሪው ህወሃት ሰራዊቱን መቋቋም ተስኖት ተሸብሯል ያሉት ጀነራል ብርሃኑ ፤እየተመዘገበ ለሚገኘው ድልና እየተፈጸመ ላለው ጀብድ መላው የሀገሪቱ ህዝብ ላሳየው አጋርነትና አኩሪ ደጀንነት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በምረቃው ስነስርዓት ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንና ሌሎችም ከፍተኛ የመንግስት ስራ አመራሮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም