በኢትዮጵያ እየተወሰዱ ያሉ የለውጥ እርምጃዎች አመርቂ ናቸው - የኦብነግ ቃል አቀባይ አዳኒ አብዱልቃድር

168
አዲስ አበባ ነሀሴ 7/2010 በኢትዮጵያ እየተወሰዱ ያሉ የለውጥ ስራዎች አመርቂ መሆናቸውን የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻ አውጪ ግንባር(ኦብነግ) ቃል አቀባይ አቶ አዳኒ አብዱልቃድር ገለጹ። በትጥቅ ትግል ላይ የነበረው የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻ አውጪ ግንባር (ኦብነግ) ትናንት ማምሻውን አዲስ አበባ ገብቷል። በግንባሩ ቃል አቀባይ አዳኒ አብዱልቃድር የተመራው ልዑክ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ካሳሁን ጎፌ እና ሌሎች የመንግስት የስራ ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውለታል። ኦብነግ አሁን የመጣበት ዓላማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በውጭ ላሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥሪ ባቀረቡት መሰረት ምላሽ ለመስጠትና ሰላማዊ ትግሉን ለመቀላቀል እንደዚሁም በሱማሌ ክልል ያለውን ግጭት ለማረጋጋት መሆኑም ተገልጿል። የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻ አውጪ ግንባር(ኦብነግ) ቃል አቀባይ አቶ አዳኒ አብዱልቃድር በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ እየተካሄዱ ያሉ የለውጥ ስራዎች ተጨባጭ ውጤት እያሳዩ መሆናቸውን ይገልጻሉ። ኢትዮጵያ በለውጥ ጎዳና ላይ እንደምትገኝና የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ መደረጋቸው እንዲሁም የዜጎች ሰብዓዊ መብት እንዲከበር እየተሰራ ያለው ስራ አበረታች እንደሆነም ጠቅሰዋል። ኦብነግ እየተካሄዱ ያሉ የለውጥ ስራዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ወደ ሀገር ገብቶ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል መወሰኑንም ገልጸዋል። እንደ ቃል አቀባዩ ገለጻ ግንባሩ በተናጥል የተኩስ አቁም ያደረገበት ዋነኛው ምክንያት በሱማሌ ክልል ያለው ግጭትና ረብሻ እንዲቆም መንግስት እያከናወነ ላለው ስራም የበኩሉን ድርሻ ለመወጣትና "ከህዝባችን ጎን መቆማችንን ለማሳየት ነው" ብለዋል። ልዑኩ በሶማሌ ክልል ሰላም እንዲሰፍን ወደ ስፍራው በመሄድ የማረጋጋት ስራ እንደሚሰራና ከመንግስት ጋር ውይይት እንደሚያደርግም ገልጸዋል። ከተለያዩ አካላት ጋር ውይይት በማድረግ ግንባሩ በሁለት ቀናት ጊዜ ውስጥ መግለጫ እንደሚያወጣም ጠቁመዋል አቶ አዳኒ። የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ካሳሁን ጎፌ በበኩላቸው ኦብነግ የጦርነትን አማራጭ ትቶ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ወደ አገር ውስጥ መግባቱ ኢትዮጵያ እያከናወነችው ላለው የለውጥ ስራ ትልቅ ትርጉም እንዳለው ገልጸዋል። ግንባሩ መንግስት ያቀረበውን ጥሪ ተቀብሎ ለኢትዮጵያ ፓለቲካ ምህዳር መስፋት አስተዋጽኦ ለማድረግ መወሰኑ እንደሚያስመሰግነውና በዚህም መንግስት ደስተኛ እንደሆነም ተናግረዋል አቶ ካሳሁን። ኦብነግ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሽብርተኛ ከተባሉ ቡድኖች መካከል አንዱ እንደነበር አስታውሰው መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ባለው ቁርጠኛ ፍላጎት በምክር ቤቱ ሽብርተኛ የተባሉ ቡድኖች ውሳኔው እንዲሻርላቸው ማድረጉን ጠቅሰዋል። የኦብነግ ተኩስ ማቆም በሱማሌ ክልል ያለውን ግጭት አርግቦ ክልሉ ወደ ቀድሞው ሰላም እንዲመለስ እየተደረገ ላለው ጥረት የበኩሉን አስተዋጽኦ ያደርጋል ብሎ መንግስት እንደሚያምን ገልጸዋል። የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይን ጥሪ ተቀብለው የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን አስታውሰው መንግስትም ፓርቲዎቹ ለዴሞክራሲው ስርዓት ግንባታ አስተዋጽኦ እንደሚያበርክቱ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል ሚኒስትር ዴኤታው። የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰኔ 28 ቀን 2010 ዓ.ም ባካሄደው 34ኛ መደበኛ ስብሰባው የኦጋዴን ብሄራዊ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦብነግ) የሽብርተኝነት ፍረጃ መሰረዙ ይታወሳል። ምክር ቤቱ በ2003 ዓ.ም ኦነግ፣ ኦብነግና ግንቦት 7ን የሽብርተኛ ቡድን ብሎ መፈረጁ የሚታወስ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሹመታቸው ጸድቆ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በተለያዩ መስኮች የለውጥ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛሉ። ለውጡን የተመለከቱ የኢትዮጵያ ህዝቦችም ከውስጥም ከውጭም ሆነው ሰፊ ድጋፍ በመስጠት ላይ ናቸው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም