የሲዳማ ክልልን በመንግስት መስሪያ ቤቶች አገልግሎት አሰጣጥ ሞዴል ለማድረግ እየተሰራ ነው

271

ሐዋሳ፣ ነሐሴ 28/2013 (ኢዜአ) የሲዳማ ክልልን በመንግስት መስሪያ ቤቶች አገልግሎት አሰጣጥ ሞዴል ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ደስታ ሌዳሞ አስታወቁ።

በክልሉ አገልግሎት አሰጣጥ፣ በገጠር ቀበሌ አስተዳደር ማጠናከሪያ ፕሮጀክት፣ የወረዳና የከተማ አስተዳደር መዋቅሮችን መልሶ ለማስተካከል በተካሄዱ ጥናቶች ላይ የውይይት መድረክ ትናንት በሀዋሳ ተካሂዷል ።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ደስታ ሌዳሞ በመድረኩ ላይ እንዳስታወቁት ክልሉን በመንግስት መስሪያ ቤቶች አገልግሎት አሰጣጥ የተሻለ ለማድረግና የህብረተሰቡን የአገልግሎት አሰጣጥ እርካታ ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው።

ብልጽግናን ለማረጋገጥና ፈጣን እድገት ለማምጣት የሕዝቡን እርካታ በተጨባጭ እውን ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

ክልሉን በመንግስት መስሪያ ቤቶች አገልግሎት አሰጣጥ ሞዴል ለማድረግ የተያዘውን ራዕይ ለማሳካት ጥናት መካሄዱን አቶ ደስታ አስታውቀዋል።

“አገልግሎት አሰጣጥን ማሻሻል ህዝቡ በተለያዩ የልማት ዘርፎች ግልፅ፣ ቀልጣፋና ፍትሃዊ አገልግሎት የማግኘት መብቱን ለማስከበር ያስችላል “ብለዋል።

የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችም ቀልጣፋ፣ ፈጣንና ወጪ ቆጣቢ አገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት ለመዘርጋት የተጀመረውን የ10 ዓመት መሪ እቅድ በስኬት ለማጠናቀቅ እንዲሰሩ ርዕሰ መስተዳደሩ አሳስበዋል።

የሲዳማ ክልል ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሀገረፅዮን አበበ በበኩላቸው የፍትሃዊነትና የቀልጣፋ አገልግሎት አሰጣጥ አለመስፈን ሕዝብን ከሚያማርሩ ጉዳዮች አንዱ መሆኑን አመልክተዋል።

“በክልሉ በአገልግሎት አሰጣጥ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት በተለይ ተአማኒነት ያለው አሰራር ማስፈንና የገጠሩ ሕዝብ የሚፈለገውን አገልግሎት ማስፋት ያስፈልጋል” ብለዋል።

ለተግባራዊነቱ የገጠር ቀበሌ አስተዳደር ማጠናከሪያ ፕሮጀክት መቀረጹን ያመለከቱት ወይዘሮ ሀገረፅዮን ፕሮጀክቱ ለቀልጣፋና ዘመናዊ አገልግሎት መስፈን እንዲሁም ለቀጣይ የልማት ሥራዎች የተደራጀና የተቀናጀ ጠንካራ አቅም እንደሚሆን አስረድተዋል።

መድረኩ በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድ በሚስተዋሉ ችግሮች ዙሪያ በመምከር ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀትና ተጠያቂነት ያለው አሰራር ለመዘርጋት ታስቦ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

በተጨማሪም መድረኩ በመዋቅር ረገድ የህዝብን ቁጥር፣ የመልማት እድልን፣ የሚመነጨውን ገቢ ታሳቢ ባደረገ መልኩ የሰው ኃይል የማሟላት፣ የወረዳና የከተማ አስተዳደር መዋቅሮችን መልሶ ለማስተካከል በተካሄደ ጥናት ላይ ግብዓት ለማሰባሰብ መሰናዳቱን አብራርተዋል።

ለአንድ ቀን በተዘጋጀው መድረክ ላይ ከክልል፣ ከዞንና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ የካቢኔ አባላትና ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።