ለዘማች ቤተሰቦች የእንክብካቤ ድጋፎች እየተደረጉ ነው

57

ደብረ ማርቆስ፣  ነሐሴ 28/2013 (ኢዜአ) በምስራቅ ጎጃም ዞን ለህልውና ዘመቻው በግንባር ለተሰማሩ የአካባቢ ሚሊሻዎች የእርሻ እና ቤተሰባቸው የእንክብካቤ ሥራ እየተካሄደ ነው።

በዞኑ ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ እምቢያለ አለኽኝ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የአካባቢው ሚሊሻዎች የሀገራቸውን ህልውና ለማስጠበቅ ወደ ጦር ግንባር ዘምተዋል።

ህብረተሰቡን በማስተባበር የዘማች ሚሊሻዎች ከ2 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የእርሻ ሥራና የለማ ሰብል እንክብካቤ እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል።

"በእዚህም የእርሻ መሬታቸውን በዘር ከመሸፈን ባለፈ የደረሰ ሰብልን ከአረም ለማጽዳት የእንክብካቤ ሥራ እየተካሄደ ይገኛል" ብለዋል።

ለእርሻ ስራው ከ10 ሺህ ብር በላይ ገንዘብ በማሰባሰብ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር እንዲሟላለቸው መደረጉን ያመለከቱት አቶ እምቢያለ፤ የሁለት ዘማች ቤተሰቦች መኖሪያ ቤትም መታደሱን ጠቅሰዋል።

ለዘማቾች የተጀመረው ድጋፍ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመው፣ በዚህ በጎ ሥራም ከ14 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች መሳተፋቸውን ተናግረዋል።

በዞኑ የባሶሊበን ወረዳ ኮርክ ቀበሌ  አርሶ አደር ይስማው ማማሩ በበኩላቸው ፤ ሀገራቸውን እና ህዝባቸውን በማስቀደም ቤቴ ልጆቼ ሳይሉ በግንባር ለተሰለፉ ሚሊሻዎች ማሳቸው ከማንም በፊት እንዲለማ መደረጉን ገልጸዋል።

በቀጣይም ሰብሉን የማረም፣ የመንከባከብና መሰል የእርሻ ሥራዎችን ለማከናወን ዘግጁ ናቸው።

በተጨማሪም ቤተሰቦቻቸውን እና የቤት እንስሶቻቸውን በአደረጃጀቶቻቸው በኩል በመንከባከብ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።

"ለህልውና ዘመቻው በግንባር የተሰለፉ ሚሊሻዎች መሬታቸውን በደቦ እያለማን ነው" ያሉት ደግሞ በአነደድ ወረዳ የእነችፎ ቀበሌ አርሶ አደር አየነው በቀለ ናቸው።

ወደ ግንባር ለሄዱት ጀግና ሚሊሻ ቤተሰቦች የተለያየ ድጋፍና እንክብካቤ በማድረግ አብሮነታቸውን እያሳዩ ነው።

በአዲሱ ዓመት ልጆቻቸው የደንብ ልብስ እና የትምህርት ቁሳቁስ እንዳይቸግራቸው በዕድር በኩል ከ10 ሺህ ብር በላይ ለመለገስ መወሰኑን አስታውቀዋል።

ድጋፍ ከተደረገላቸው የሚሊሻ አባላት ቤተሰቦች መካከል በአነደድ ወረዳ የንፋሳም ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ እናት አገኘሁ ይርዳው አንዱ ናቸው።

"ባለቤቴ የሀገሩን ዳር ደንበር ለማስከበር ወደ ጦር ግንባር ቢሄድም የአካባቢው ማህበረሰብ አይዞሽ ከጎንሽ ነኝ በማለት እያበረታታኝ ነው'' ብለዋል።

ከግማሽ ሄክታር በላይ የእርሻ መሬታቸው በአካባቢው ነዋሪዎች ድጋፍ ማደበሪያ ጭምር በመጠቀም በጤፍ ዘር መሸፈኑን ተናግረዋል።

በምስራቅ ጎጃም ዞን ወደ ግንባር ከሄዱት የሚሊሻ አባላት መካከል ከ1ሺህ 440 በላይ ለሚሆኑት የማሳ እንክብካቤ እና የዘር ሥራ ተከናውኗል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም