የለውጡ ማግስት ፈተናና ተስፋ - ከምሁራኑ አንደበት

84

ነሐሴ 27 ቀን 2013 (ኢዜአ) ከአገራዊ ለውጥ ማግስት ጀምሮ ኢትዮጵያዊያን ከተፈጥሯዊ እሴቶታቸው የሚቀዳውን ህብረ-ብሔራዊ ወንድማማችነት በማጎልበት በርካታ ስኬቶችን ያስመዘገቡበት እንደነበር ምሑራኑ ይናገራሉ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ተመራማሪው ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው እና ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ ኢትዮጵያ በለውጥ ማግስት የገጠሟት ፈተናዎችና ተስፋዎቿን በሚመለከት ለመገናኛ ብዙኃን ሐሳባቸው ሰጥተዋል።

ምሑራኑ ኢትዮጵያዊያን በለውጥ ማግስት የገጠሟቸውን ፈተናዎች በጠንካራ አገራዊ አንድነት በመወጣት ህብረብሔራዊ ወንድማማችነታቸውን ያጎሉበት ወቅት ነው ብለዋል።

በሉዓላዊነት ላይ የተቃጣውን አገር የማፍረስን ተግባር ለማጥፋት የወሰዱት የአንድነት ወኔም የሚደነቅ እንደሆነ አንስተዋል።

"የአገር ሉዓላዊነት ሲጠበቅ ነው ምንም ነገር ማድረግ የሚቻለው" በሚል አሸባሪውን ህወሓት ለማጥፋት በተያዘው ዘመቻ እንደ አብን፣ ኢዜማና ሌሎችም የፖለቲካ ፓርቲዎች የወሰዱት ተነሳሽነት በታሪክ የማይዘነጋ ተግባር መሆኑን ጠቅሰዋል።

የዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ኢትዮጵያ የያዘችውን የህልውና ተጋድሎ በቅጡ እየተረዱት መምጣታቸውን የሚያመላክቱ ጉዳዮች እንዳሉ ምሁራኑ ገልጸዋል።

የበለጠ ግልጸኝነትን ለመፍጠርም ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ላይ የበለጠ መስራት እንዳለባት መክረዋል።

ኢትዮጵያዊያንም ከተፈጥሯዊ እሴታቸው የሚቀዳውን ህብረብሔራዊ ወንድማማችነት በጽኑ አንድነት በማስቀጠል የአገራቸውን ሉዓላዊ የግዛት አንድነት ማስጠበቅ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

የፍልስፍና ምሑሩ ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ፤ "ብልጽግና ፓርቲ ኢትዮጵያን በለውጥ ጎዳና በማስገባት መምራት በጀመረበት ማግስት በርካታ ስኬት ሲያመጣ ፈተናም ገጥሞታል" ብለዋል።

ኢትዮጵያዊያንን እርስ በእርስ በማጋጨት አገርን ለማፍረስ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች እረፍት የለሽ እንቅስቃሴ ለለውጡ ከባድ ፈተና ሆኖ እንደነበር ጠቁመዋል።

የጠቅላላ አገራዊ ምርጫው በሰላም መጠናቀቅ፣ ከብሔረሰቦች የአብሮነት እሴት የሚቀዳው ኢትዮጵያዊነት አብቦ የወጣበት ክስተት መፈጠር ትልቁ ስኬት እንደነበረም አስታውሰዋል።

ከስኬቶቹ የሚልቀው ግን የኢትዮጵያዊያን ፕሮጀክት ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የደረሰበት ደረጃ መሆኑን  ተናግረዋል።

"የምዕራቡን ዓለም ተጽዕኖ በመቋቋም ከዓመታት በፊት በኢትዮጵያ የውጭ ፖሊሲ ሊታሰብ የማይችልን እድል የፈጠሩት የብልጽግና መሪ ምስጋና ይገባቸዋል" ብለዋል።

የታሪክ ተመራማሪ እና ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው፤ ኢትዮጵያ ከመጋቢት 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ዘርፈ ብዙ እድሎችን አግኝታ ያተረፈችባቸውን ያህል ከኋላ የመጡ ውዝፍ ፈተናዎች በብዙ መንገድ መንግሥትን ፈትነው እንደነበር አንስተዋል።

በለውጥ ማግስት እንደ ፍርድ ቤት፣ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድና ሌሎችም የፍትህ ተቋማት ላይ በተቻለው መጠን ማሻሻያ መደረጉ በበጎ ጎኑ የሚነሳ ተግባር እንደሆነም አመላክተዋል።

አፍርሶ ከመስራት አባዜ በመውጣት ካለፈው ትምህርት እየተወሰደ ነገን በተሻለ እይታ የመመልከት እድል መፈጠሩ ትልቁና ኢትዮጵያ አይታ የማታውቀው ወርቃማ እድል እንደሆነ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያዊያን መፍትሄው አንድነትን ማጽናት መሆኑን በመረዳት አሁን እያሳዩት ያለውን የአርበኝነት ወኔ በማስቀጠል ለአገራቸው ሉዓላዊነት መጠበቅ መትጋት አለባቸው ሲሉ የፍልስፍና ምሑሩ ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም