ዜጎች በክልሉ ለሚካሄደው 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ

72

ነሀሴ 27 ቀን 2013 (ኢዜአ) በሀረሪ ክልል ለሚካሄደው 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ዜጎች ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር  ኦርዲን በድሪ ጥሪ አቀረቡ።

በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲወለድ የዜጎች ንቁ ተሳትፎ እጅግ ወሳኝ መሆኑን ነው ርዕሰ መስተዳደሩ የገለፁት።

የ6ኛው ብሔራዊ ምርጫ ሂደት ነጻ፣ ፍትሐዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ሰላማዊ እንዲሆን የክልሉ መንግስት በቁርጠኝነት እየሠራ እንደሚገኝም አክለው ገልጸዋል።

የክልሉን ምርጫ አስመልክቶ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በወሰነው መሰረት በሀረሪ ክልል በጀጎል ዙሪያ እና ሁንዴኔ የምርጫ ክልል በድጋሚ የመራጮች ምዝገባ ከነሀሴ 26 እስከ ጳጉሜ 5 ቀን 2013ዓ.ም ድረስ የሚቆይ የመራጮች ምዝገባ እየተካሄደ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ቦርዱ በጀጎል ዙሪያ እና ሁንዴኔ የምርጫ ክልል በድጋሚ የመራጮች ምዝገባ እንዲካሄድ በወሰነው መሰረት በሸንኮር ፣ አቦከር ፣ ሀኪም ፣ ጅንኤላ ፣ ሶፊ ፣ ድሬ ጠያራ እና በኤረር ወረዳ ነዋሪዎች ከዚህ ቀደም የወሰዱት የምርጫ ካርድ አገልግሎት ስለማይሰጥ በድጋሚ በየአካባቢው ባሉ የምርጫ ጣቢያዎች በመሄድ በአዲስ ተመዝግበው የመራጭነት ካርድ መውሰድ እንዳለባቸው ገልጸዋል።

እንዲሁም በጁገል ልዩ ምርጫ ክልል ከጳጉሜ 1 እስከ 5 ቀን 2013 ተጨማሪ ምዝገባ እንደሚካሄድ ገልጸው፤ ህብረተሰቡም በየአካባቢው በሚገኙ ምርጫ ጣቢያዎች የተቀመጠው የጊዜ ገደብ ሳይጠናቀቅ የመራጭነት ካርድ እንዲወስዱ ጠይቀዋል።

ከክልሉ ውጪ የሚኖሩ የሀረሪ ብሔረሰቡ ተወላጆች የሚመርጡባቸው የምርጫ ጣቢያዎች አዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ፣ በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል ( አዳማ ፣ ጭሮ ፣ ኮምቦልቻ ፣ ጉርሱም ፣ ፈዲስ ፣ ደደር እና ሃሮማያ) ፣ ድሬዳዋ ከተማ መስተዳድር ፣ እና በሶማሌ ብሔራዊ ክልል ጅግጅጋ ከተማ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ የምርጫ ካርድ በመውሰድ ዴሞክራሲያዊ መብታችሁን በአግባቡ ልትጠወሙበት ይገባል በማለት ገልጸዋል።

በሕገ መንግሥታችን አንቀጽ 38 ሁሉም ኢትዮጵያዊ የመምረጥና የመመረጥ መብት እንዳለው ይደነግጋል ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ፤ “የሀገራችንን የነገ ዴሞክራሲ ለመወሰን ፣ ዛሬ የመራጮች ምዝገባ መታወቂያ ካርድ እናውጣ ፤ ካርድ ለማውጣት ነገ አትበሉ ፤ ነገ ከዛሬ ይጀምራል” ሲሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

በተጨማሪ ሁሉም አካላት ምርጫው በታቀደለት የጊዜ ገደብ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ማሳሰባቸውን ከሀረሪ ክልል መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ያተገኘው መረጃ  ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም