አብቁተና ሰራተኞቹ ለህልውና ዘመቻው 81 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረጉ

50

ባህር ዳር ፤ ነሐሴ 27/2013 (ኢዜአ) የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም /አብቁተ/ እና ሠራተኞቹ ለህልውና ዘመቻው ድጋፍ የሚውል 81 ሚሊዮን ብር አበረከቱ።

የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መኮንን የለውምወሰን ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት ለዘመቻው ተቋሙ 25 ሚሊዮን ብር፤ የተቋሙ ሠራተኞች ደግሞ 56 ሚሊዮን ብር ለግሰዋል።

የተቋሙ ሠራተኞች ድጋፉን ያደረጉት የአንድ ወር ደመወዛቸውን  እንደሆነም አመልክተዋል።

ሠራተኞቹ በግንባር ለተሰለፉት የጸጥታ ኃይሎች 45 ኩንታል በሶ ማዘጋጀታቸውንም ጠቅሰዋል።

ከድጋፉ በተጨማሪ በርካታ የተቋሙ  ሠራተኞች የመንግሥትን የክተት ጥሪ ተቀብለው አሸባሪውን ህወሃት በግንባር እየተፋለሙ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

ተቋሙ ወደ ግንባር ለዘመቱት ሠራተኞቹ ሙሉ ደመወዝና ጥቅማ ጥቅማቸውን ዘመቻው በድል እስኪጠናቀቅ ድረስ እንደሚሰጥ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አረጋግጠዋል።

አሸባሪ የህወሃት ቡድኑ በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች 90 የተቋሙ ጽህፈት ቤቶች ንብረት ጉዳት ማድረሱንና ከነዚህም አንድ ጽህፈት ቤት በሙሉ በሙሉ መውደሙን አውስተዋል።

አሸባሪውና ወራሪው የህወሃት ቡድን በአማራና አፋር ክልሎች በከፈተው ጦርነት በሰው ሕይወት፣በንብረትና በእንስሳት ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም