በሀገሪቱ ለአርሶ አደሮች ለማዳረስ የሚያስችል ዲጂታል የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት ቴክኖሎጂ ተግባራዊ ተደረገ

76

አዳማ፣ ነሐሴ 27/2013( ኢዜአ) በሀገሪቱ ከ5 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮችን ለማዳረስ የሚያስችል ዲጂታል የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት ቴክኖሎጂ ተግባራዊ ማድረጉን የግብርና ሚንስቴር አስታወቀ።

አዲሱን የግብርና ፍኖተ ካርታ ውጤታማ ማድረግና በዘርፍ ተቋማዊ ለውጥ ማምጣት በሚቻልበት ላይ ዛሬ በአዳማ ከተማ የምክክር መድረክ ተካሂዷል።

የግብርና ሚኒስቴር አማካሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ኢፋ ሙለታ በወቅቱ እንዳሉት፤ ቴክኖሎጂው ለአርሶ አደሩ በተንቀሳቃሽ  ስልክ፣ ታብሌቶችና ሌሎች  ዘዴዎች የመረጃ ልውውጥ፣ የስልጠናና ምክር  አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ነው።

በዚህም በሀገሪቱ ከ5 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ አርሶ አደሮች  አገልግሎቱን ለማዳረስ   የሚያስችል ቴክኖሎጂ ተግባራዊ መደረጉን አስታውቀዋል።

ለአገልግሎቱ  የሚያግዙ  ከ34 ሺህ በላይ ታብሌቶች ተገዝተው መሰራጨታቸውን ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸው፤ ሳይቆራረጥ ለአርሶ አደሩ እንዲደርስ ያደርጋል ነው ያሉት።


ቴክኖሎጂው ግብርናውን ለማዘመን መሰረት መሆኑን አመልክተው፤ አሁን ሀገሪቱ ባላት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና የኔትወርክ ሽፋን ስራው በተሻለ ደረጃ ማስኬድ እንደሚቻልና መደላድል መኖሩንም ተናግረዋል ።


የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጄንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሴ በበኩላቸው፤  ቴኖክሎጂው በተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተበታተነ መልኩ የሚሰጠውን የግብርና ዲጂታል ኤክስቴንሽን አገልግሎት በኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ በማስደገፍ በተቀናጀ መልኩ ለመስጠት የሚያስችል ነው ብለዋል።

በሀገሪቷ ከ30 በላይ የሚሆኑ  የግብርና ዲጂታል  ኤክስቴንሽን አገልግሎት ላይ የሚሰሩ ድርጅቶች አሉ ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ በዚህም በአንድ ቦታ ላይ ተመሳሳይ አገልግሎት በተለያዩ አካላት በመስጠት የሀብት ብክነት ማስከተሉን ጠቅሰዋል።


አዲሱ የዲጂታል የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት ደረጃውን የጠበቀና ወጥነት ያለው በአንድ ስትራቴጂ የሚመራ የተቀናጀ ቴክኖሎጂ  የሚያመቻች  ፎረም ለመመስረት እንደሆነም ጠቁመዋል።


"በተለይ ምርታማነትን በእጥፍ ለማሳደግ የተቀመጠውን ግብ አሁን በሚሰጠው የኤክስቴንሽን አግልግሎት ማሳካት ስለማንችል ግቡን ለመድረስ የተቀናጀ የዲጂታል ኤክስቴንሽን አገልግሎት ስርዓት መዘርጋት በማስፈለጉ ነው" ብለዋል።


በተንቀሳቃሽ  ስልኮች፣ ታብሌቶች፣ ሬዲዮ፣ ቴሌቪዥንና ድምጽ እንዲሁም በኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ስርዓት የታገዘ አገልግሎትና ምክር ለአርሶና  አርብቶ አደሩ ይሰጣል ነው ያሉት።

የግብዓት አገልግሎት በተለይ ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያና የፀረ አረም ኬሚካልን በማመቻቸት  አርሶ አደሩ ገበያ ተኮር ምርት እንዲያመርት ከሀገር ውስጥና ከዓለም የወቅቱ ገበያ ጋር የተያያዙ የመረጃ ልውውጥ የሚደረግበት መሆኑንም አብራርተዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም