ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከኡጋንዳና ሩዋንዳ መሪዎች ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነትን ለማጠናከርና በቀጠናዊ የጋራ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል

61

ነሀሴ 27 ቀን 2013 (ኢዜአ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በኡጋንዳና ሩዋንዳ በነበራቸው ቆይታ ከፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒና ከፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነትን ለማጠናከር፣ በቀጠናዊ ብሎም አለም አቀፋዊ የጋራ ጉዳዮች ዙሪያ መምከራቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ገለጸ።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬተሪያት የውጭ ቋንቋዎችና ዲጂታል ሚዲያ ዘርፍ ሃላፊ ቢልለኔ ስዩምና የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ እየሰጡ ነው።

በዚህ ወቅት ቢልለኔ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በካምፓላ ኡጋንዳና በሩዋንዳ ኪጋሊ ያደረጉትን ይፋዊ የስራ ጉብኝነት የተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሁለቱ አገራት በነበራቸው ቆይታ ከፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒና ፖል ካጋሜ ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነትን ማጠናከር ስለሚቻልባቸው መንገዶችና የጋራ በሆኑ ቀጠናዊና አለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል ብለዋል።

የቀጠናዊ የንግድ ግንኙነትን በተመለከተም ውይይት ማካሄዳቸውን አንስተው፤ በንግድ ግንኙነትና በአጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች ላይ ያጋጠሙ ችግሮችን መሪዎቹ መምከራቸውን ገልጸዋል።

በቀጠናዊ ሰላምና ደህንነት ዙሪያም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከመሪዎቹ ጋር በነበራቸው ቆይታ ማንሳታቸውን ነው ሀላፊዋ ያብራሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም