የባለስልጣኑ አመራሮችና ሰራተኞች ለአገር መከላከያ ሰራዊት ደም ለገሱ

75

አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 27/2013(ኢዜአ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምግብ የመድኃኒት የጤና ክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለስልጣን አመራሮችና ሰራተኞች ለጀግናው መከላከያ ሰራዊት ደም ለገሱ።

የባለስልጣኑ አመራርና ሰራተኞች ከዚህ በፊት የአንድ ወር ደሞዛቸውን ለሰራዊቱ የለገሱ ሲሆን በዛሬው እለት ደግሞ ደማቸውን ለግሰዋል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ታመነ አጫሞ፤ ለአገር ውድ ህይወቱን እየከፈለ ላለው ሰራዊት ከደም መስጠት ባለፈ በሁሉም መስክ ለማገዝ ዝግጁ ነን ብለዋል።

"ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ" ብሎ የተነሳውን አሸባሪ የህወሓት ቡድን እየደመሰሰ ላለው የአገር መከላከያ ሰራዊት ደም በመለገሳችን ተደስተናል ብለዋል።

የተቋሙ ሰራተኞች የአንድ ወር ደሞዛቸውን ከመለገስ በተጨማሪ ሌሎች ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ በቁሳቁስና በአይነት ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

የአገር ህልውናን ለማስጠበቅ እየተፋለመ ላለው ሰራዊት ደም ከመስጠት ባለፈ ተጨማሪ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነን ብለዋል አስተያየታቸውን የሰጡት ሰራተኞች።

የቦሌ ክፍለ ከተማ የምግብ የመድኃኒት የጤና ክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ፋንታነሽ ሰለሞን ሰራዊቱ ቤተሰቡን ትቶ ለአገር አንድነት ሲል አሸባሪውን ቡድን እየተፋለመ ላለው ሰራዊት ድጋፋችን ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ አረጋግጠዋል።

ከድጋፍ በተጨማሪ ለአገራችን እስከ ህይወት መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን ብለዋል።

የአገር መከላከያ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ለሰራዊቱ እስካሁን 3 ቢሊዮን ብር ገቢ የተሰበሰበ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 42 ሚሊዮን ብር ከዲያስፖራው የተገኘ ነው።

ከዚህም በተጨማሪ ከ6 ሺህ 600 በላይ ሠንጋዎች፣ ከ10 ሺህ በላይ በግና ፍየሎች፣ በርካታ ብር ግምት ያለው ደረቅ ሬሽን ለሠራዊቱ መሰብሰቡን ይፋ አድርጓል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም