የአሸንዳ በዓል ከባህላዊ ይዘቱ ባለፈ የገቢ ማስገኛ ሆኖ እያገለገለ ነው፡-ነጋዴዎች

77
መቀሌ ነሀሴ 6/2010 የአሸንዳ በዓል ከባህላዊ ይዘቱ ባለፈ የገቢ ማስገኛ ሆኖ እያገለገላቸው መሆኑን በባህላዊ ልብስ ስፌት ስራ  የተሰማሩ የንግድ ማህበረሰብ አባላት ገለጹ፡፡ በባህላዊ ልብስ ንግድ ስራ የተሰማራ ወጣት ከድር አህመድ እንደገለጸው የአሸንዳ በዓል ልጃገረዶች ብቻ ሳይሆኑ  ነጋዴዎችም በጉጉት እንደሚጠብቁት  ተናግረዋል፡፡ ይህም በዓሉን ተከትሎ  የሚፈጠረው የባህላዊ አልባሳት ግብይት በሳምንት እስከ 4ሺህ ብር ትርፍ  እንደሚያገኝ ተናግረዋል፡፡ ‘‘የአሸንዳ በዓል ሲነሳ ኢትዮጵያዊ ባህል፤ ታሪክና ማንነት አብሮ ይነሳል'' ያሉት ደግሞ በመቀሌ ከተማ  የቅሳነት ባህላዊ አልባሳት መሸጫ መደብር ባለቤት አቶ አሸናፊ ፀጋይ ናቸው፡፡በባህላዊ አልባሳት ንግድ ስራ የተሰማሩ የንግዱ ማህበረስብ ከአንድ ልብስ እስከ 200 ብር ትርፍ እንደሚያገኙበት ተናግረዋል፡፡ የአገር ባህል ልብስ  በውጭ አገርም ተፈላጊነቱ እየጨመረ በመምጣቱ ባህላችንና ገጽታችን የምናስተዋወቅበት ዘርፍ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በጥልፍ ሙያ ስራ የተሰማራችው ወጣት ኪዳን በርኸ በበኩሏ የአሸንዳ በዓል ልጃገረዶች በነጻነት ወጥተው ባህላቸውን በተለያዩ መንገዶች የሚገልጽበት ከመሆኑ ባለፈ በተሰማራችበት ሞያ ገቢ የምታገኝበት መሆኑን ገልጻለች፡፡ የአሸንዳ ሳምንት ሌት ተቀን የጥልፍ ስራ በመስራትና ለባህላዊ ልብስ አመራቾች በማስረከብ  በወር እስከ አራት ሺህ ብር ገቢ  እንደምታገኝ ተናግራለች፡፡ ለአሸንዳ በዓል  በ1 ሺህ 800 ብር ልብስ መገዛቷን የተናገረችው ደግሞ ወጣት አስቴር ተክላይ ናት፡፡ በዓሉ ለልጃገረዶች ባህላዊና  ልዩ አጋጣሚ በመሆኑ በድመቀት ለማክበር ዝግጅት ላይ መሆኗን ተናግራለች፡፡ የትግራይ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ ወይዘሮ ኢትዮጵያ ህሉፍ በበኩላቸው የአሸንዳ በዓል ሴቶች በባህላዊ አልባሳት ደምቀውና ሽሩባ ተሰርተው በዓሉን በድምቀት ለማክበር ዝግጅት በማድረግ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ከባህላዊ እሴቱ ዜጎች ኢኮኖሚያ ተጠቃሚ የሚሆኑበት መንገድም እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡                  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም