በአማራ ክልል አሸባሪው ህወሃት በያዛቸው አካባቢዎች ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች ለተጎጂዎች እርዳታ እያደረሱ አይደለም

70

ነሐሴ 26 ቀን 2013 (ኢዜአ) በአማራ ክልል አሸባሪው ህወሃት በያዛቸው አካባቢዎች ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች ለተጎጂዎች እርዳታ እያደረሱ አለመሆኑን የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን ገለጸ።

ከፌዴራል አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽንና ከአማራ ክልል የተወጣጡ የምርመራ ቡድን ከሰሜንና ደቡብ ወሎ እንዲሁም ከዋግ ኸምራ ዞኖች ተፈናቅለው ለሚገኙ ዜጎች ስለሚደረጉ የእርዳታ አቅርቦትና ስርጭቶች ሁኔታ ግምገማ አካሂዷል።

በግምገማውም መሰረት መንግስት የተለያዩ ተቋማትን በማስተባበር ጭምር ሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ፣ ስርጭቱ ፍትሀዊ እንዲሆን የማድረግ ስራዎችን በማከናወን ለ120 ሺህ ተፈናቃዮች ድጋፍ ማድረጉ ታይቷል።

በአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን የቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ባለሙያና የምርመራ ቡድኑ አባል አቶ ጌቴ ምሕረቴ እንደገለጹት፤ አሸባሪው ህወሃት ከወረራቸው አካባቢዎች ተፈናቅለው በደሴና ኮምቦልቻ ለሚገኙ ወገኖች መንግስት ድጋፍ እያቀረበ ነው።

ሆኖም አሸባሪው ህወሃት በወረራ በያዛቸው የሰሜን ወሎ አካባቢዎች የመንግስት መዋቅር ገብቶ እርዳታ እንደማያደርስ ጠቁመው፤ ዓለም አቀፍ የእርዳታ ተቋማት በማንኛውም ሁኔታ ገብተው ለተጎጂዎች ሰብዓዊ እርዳታ ማድረስ እንደሚችሉ ተናግረዋል።

ይህን አስቻይ ሁኔታ ስላልተጠቀሙበት "በአማራ ክልል የሰሜን ወሎ አካባቢዎች እርዳታ የማድረስ ተግባር አልሰሩም" ብለዋል።

በተለይ በሰሜን ወሎ ዞን የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች አብዛኞቹ በሴፍቲኔት መተዳደራቸው ችግሩን እንዳከበደው ገልጸዋል።

አሸባሪው ህወሃት የተቸገሩትን ከመርዳት ይልቅ መሰረተ ልማት እያወደመ፣ ያለውን እየዘረፈ እንደሚሄድ አስታውሰው፤ በዚህ ምክንያት ነዋሪዎቹ የተወሳሰበ ችግር ላይ መውደቃቸውን ገልጸዋል።

አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ከዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች ውጭ "በሰሜን ወሎ ዞን የሰብዓዊ እርዳታ ቁሳቁስ ይዞ መግባት አይቻልም" የሚሉት አቶ ጌቴ፤ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችም ከተቋቋሙበት መርህ ባፈነገጠ መልኩ እርዳታ እያደረሱ አለመሆኑን አብራርተዋል።

ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች የሰብዓዊ እርዳታ ለሚሹ ወገኖች በወቅቱ ማድረስ ተግባራቸው መሆኑን አውስተው፤ "በአማራ ክልል ግን ይሄንን ለማድረግ አልደፈሩም" ብለዋል።

በሰሜን ወሎ ዞን ከመኖሪያ ቀዬአቸው ያልሸሹና በሴፍቲኔት የሚኖሩ ዜጎች የሴፍቲኔትም ሆነ አስቸኳይ ሰብዓዊ እርዳታ እየደረሳቸው እንዳልሆነ ገልጸው፤ ነዋሪዎቹ ለከፋ ችግር መጋለጣቸው አይቀሬ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች ለመርህ ተገዢ በመሆን ተጎጂዎች ባሉበት አካባቢ ድጋፉን አጓጉዘው ማድረስ እንደሚጠበቅባቸው አብራርተዋል።

ይህ ካልሆነ ግን መንግስት መድረስ በማይችልበት ሁኔታ በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ያልታወቁ "የደሀ ደሀ ተብለው በሴፍቲኔት የሚተዳደሩ ዜጎች ቶሎ ድጋፍ ካልደረሳቸው አስከፊ ረሀብና እልቂት ይከሰታል" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም