ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ 200 ሚሊዮን ብር በሆነ ወጪ የመረጃ እና የተግባቦት ቴክኖሎጂ ማዕከል ገነባ

87

ድሬዳዋ፤ ነሐሴ 26/2013(ኢዜአ) ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ 200 ሚሊዮን ብር በሆነ ወጪ ዘመናዊ የመረጃና የተግባቦት ቴክኖሎጂ ማዕከል በመገንባት ለአገልግሎት አበቃ።

በዩኒቨርሲቲው  ሀገር አቀፍ የመረጃና የቴክኖሎጂ አውደ ርዕይ ነገ ይከፈታል፡፡

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የመረጃና መገናኛ ቴክኖሎጂ ዳይሬክተር አቶ ስንታየሁ በላይ እንዳሉት፣ ተቋሙ ባለፉት ሁለት ዓመታት የመማር ማስተማር ስራውን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ ሲሰራ ቆይቷል።

በዚህም 200 ሚሊዮን ብር በሆነ ወጪ ዘመናዊና ተደራሽ የሆነ የመረጃና የተግባቦት ቴክኖሎጂ ማዕከል ገንብቶ   ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ 24 ሰዓታት አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

"ማዕከሉ ወደ ዲጂታል የመማር ማስተማር ሥራ ለመግባት የሚደረገውን ጉዞ ከማፋጠን ባለፈ ተማሪዎች የዲጂታል ቤተ-መጻህፍት ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓል" ብለዋል።

ተማሪዎች ለ24 ሰዓት ቀልጣፋ የኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚ በማድረጉም ለዓመታት ሲያነሱት የነበረውን የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ለመፍታት እንዳስቻለ አስረድተዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ ማዕከሉ ለሚቀጥሉት አስር ዓመታት አገልግሎት መስጠት የሚያስችል መሆኑ ወደ ዲጂታል ለመግባት የተያዘውን ዕቅድ ስኬታማ ለማድረግ ያግዛል።

በዩኒቨርሲቲው የጀነራል ቢዝነስ የአምስተኛ ዓመት ተማሪ ብርሃኑ ድሪባ፣ ማዕከሉ ከመገንባቱ በፊት  ፈጣን የኢንተርኔት አገልግሎት ለማግኘት ከተቋሙ ውጪ ጊዜና ገንዘቡን ያባክን እንደነበር አስታውሷል፡፡

"አሁን በማዕከሉ ዲጂታል ቴክኖሎጂውን በመጠቀም የኢንተርኔት መረጃ ከማግኘት ባለፈ እውቀት የሚሰጠንን የሙከራ ሥራዎች በቀላሉ እያከናወንን እንገኛለን" ብሏል፡፡

"የተማሪዎች የዓመታት የመልካም አስተዳደር ጥያቄ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ አለመሆን ነበር" ያለው ደግሞ የሶስተኛ ዓመት የኢንጂነሪንግ ተማሪ ጉዲና ገቢታ ነው፡፡

"ይህ ችግር ተፈትቶ ወደ ጂጂታል የመማር ማስተማር ዘመን እየገባን መሆኑን ጥሩ ነው"  ብሏል፡፡

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደቻሳ ጋንፉሬ በበኩላቸው፤ ሀገር አቀፍ የመረጃና የቴክኖሎጂ አውደ ርዕይ እንደሚከፈት አስታውቀዋል፡፡

ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በሚካሄደው በተዘጋጀው አውደ ርዕይ  የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የዘርፉ ምሁራን እና ባለሙያዎች እንደሚሳተፉ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም