በጀግንነት ሲፋለሙ ለተሰው ቤተሰቦች ማቋቋሚያ አንድ ባለሀብት የገንዘብ ድጋፍ አደረጉ

94

ጎንደር ፤ ነሐሴ 25/2013 (ኢዜአ) በጎንደር ከተማ የሚገኙ አንድ ባለሀብት አሸባሪው የህወሓት ቡድንን በግንባር ሲፋለሙ በጀግንነት ለተሰዉ ቤተሰቦች ማቋቋሚያ የሚሆን 200 ሺህ ብር የሚጠጋ የገንዘብ ድጋፍ አደረጉ፡፡

ድጋፉን ያደረጉት የጎንደር ከተማ ነዋሪ አቶ አህመድ ኑሩ የተባሉ ባለሃብት ሲሆኑ ድጋፉም የመንግስትን የክተት ጥሪ ተቀብለው ለሃገራቸው ክብር ሲሉ በጀግንነት ለተዋደቁ የቤተሰብ አባላት የሚውል ነው።

ባለሀብቱ ከለገሱት ገንዘብ 150ሺህ ብር ለቤተሰቦች ማቋቋሚያ እንዲሁም 35ሺህ ብር ደግሞ ለአዲስ ዓመት የዘመን መለወጫ በዓል መዋያ እንደሚሆን ታውቋል።

"ለሀገር ክብርና ነጻነት እንዲሁም ለህዝብ ደህንነት ሲሉ መተኪያ የሌለውን ህይወታቻውን ለሰጡ ጀግኖች ቤተሰብ ከገንዘብ በላይ ሌላም ድጋፍ ማድረግ ያስፈልጋል" ሲሉም ባለሃብቱ ተናግረዋል።

ድጋፍ ከተደረገላቸው ቤተሰቦች መካከል አቶ ጌጡ ማነገረው "ወንድማችን የሽብር ቡድኑን ሲፋለም በጀግንነት መሰዋቱ የክብር ሞት ነው" ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ባለሀብቱ በተቆርቋሪነት ተነስተው ለቤተሰቡ ባደረጉት ድጋፍ መደሰታቸውን ጠቅሰው፤ ወቅቱ የመደጋገፍና የመረዳዳት ጊዜ በመሆኑ ሌሎችም የባለሀብቱን ፈለግ እንዲከተሉ ጠይቀዋል፡፡

አቶ ገበየሁ እንየው በበኩላቸው ''ወንድሜ የሽብር ቡድኑን በጀግንነት ሲዋጋ ህይወቱን ቢያጣም ለእናት ሀገሩ ነጻነትና ክብር ሲል መስዋዕት የከፈለ በመሆኑ ክብር ይሰማኛል'' ብለዋል፡፡

ባለሀብቱ በህልውና ዘመቻው መስዋዕት የሆኑ ጀግኖችን በማስታወስ ለቤተሰቦቻቸው ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም