የኩላሊት ህሙማን ህክምናቸውን መከታተል እንዲችሉ ድጋፍ እንዲደረግ ተጠየቀ

154

ነሐሴ 25/2013 (ኢዜአ) የኩላሊት ህመምተኞች እጥበት በጎ አድራጎት ድርጅት የኩላሊት ህሙማን ህክምናቸውን በአግባቡ መከታተል እንዲችሉ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠየቀ፡፡

ድርጅቱ ለኩላሊት ህሙማን የሚደረገውን ድጋፍ አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥቷል።

የድርጅቱ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን አሰፋ በመግለጫቸው የኩላሊት ህሙማን ህክምናቸውን መከታተል እንዲችሉ ድጋፍ እንዲደረግ ጠይቀዋል።

በገንዘብ እጦት ምክንያት እየተሰቃዩ ላሉ ወገኖች ለመድረስ የሚደረገው እንቅስቃሴ መጠናከር አለበት ብለዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ጽህፈት ቤት ከአንድ ዓመት በፊት ለ110  ሰዎች ፈቅዶት የነበረው የነጻ የኩላሊት እጥበት በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን ጠቅሰው ለኩላሊት ህሙማን በቀጣይም ልዩ ትኩረት መስጠት ይገባል ብለዋል።

በርካታ የኩላሊት ህሙማን በኢኮኖሚና ሌሎችም ችግሮች ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ እየገቡ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

በመሆኑም በጤና ሚኒስቴር በኩል እንዲገዙ የተፈቀዱ 100 ማሽኖች ጉዳይ አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።

የኩላሊት ህሙማንን በማገዝ፣ በመደገፍና እንክብካቤ በማድረግ ሁሉም እንዲተባበር ጥሪ ቀርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም