በግንባር እየተዋደቁ ለሚገኙ ጓዶቻችን ደም ከመስጠት እስከ የሕይወት መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን

301

ሀዋሳ፤ ነሐሴ 25/2013(ኢዜአ) በግንባር እየተዋደቁ ለሚገኙ ጓዶቻችን ደም ከመስጠት ባለፈ ከጎናቸው ቆመን የሕይወት መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን ሲሉ በሀገር መከላከያ ሠራዊት የደቡብ ዕዝ አባላትና ሲቪል ሠራተኞች አስታወቁ።

መቶ አለቃ ሽመልስ መኮንን ከሌሎች የዕዙ አባላትና ሲቪል ሠራተኞች ጋር በመሆን በግንባር እየተዋደቁ ላለው ሠራዊት ደም ለግሰዋል።በዚህ ወቅት በሰጡት አስተያየት “ራስን ለመስዋዕትነት አሳልፎ በመስጠት ኢትዮጵያን ማኖር የሁላችንም የዜግነት ግዴታ ነው” ብለዋል።

ኢትዮጵያዊያን ህብረታቸውን አጠናክረው በአንድነት ከተነሱ የማያሸንፉት የውጭም ሆነ የሀገር ውስጥ ጠላት እንደማይኖርም ተናግረዋል።“በግንባር እየተዋደቁ ለሚገኙ ጓዶቻችን ደም ከመስጠት ባለፈ ከጎናቸው ቆመን የሕይወት መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን” ሲሉ አስታውቀዋል።

የወታደር ተቀዳሚ እሴቱ ከራስ በፊት ሀገር የሚል መርህ እንደሆነ የተናገሩት ሀምሳ አለቃ ብርሀኑ ጉርሜሳ በበኩላቸው፣ “ለሀገር በጀግንነት እየተዋደቀ ላለው ጓዴ ደም መለገስ ብቻ ሳይሆን ለመሞትም ቁርጠኛ ነኝ” ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያዊያን በግንባርም ሆነ በአካባቢያቸው ያለልዩነት ለሀገር ህልውና እያደረጉ ያሉት ተጋድሎ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ሀምሳ አለቃ ብርሀኑ ተናግረዋል።

ከደቡብ ዕዝ ሲቪል ሠራተኞች መካከል ወይዘሮ ሙሉነሽ ማርቆስ በበኩላቸው፤ “ለእኛ ብሎ የሕይወት መስዋዕትነት እየከፈለ ለሚገኘው ሠራዊታችን ደም የምለግሰው በደስታ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።በገንዘብም ሆነ ግንባር ድረስ በመዝመት ለወገን ጦር ስንቅ ለማቀበል መዘጋጀታቸውንም አስታውቀዋል።

በሀገር መከላከያ ሠራዊት የደቡብ ዕዝ ሴቶች ጉዳይ ቡድን መሪ ኮሎኔል ፋንታነሽ ሞላ ፤ ፣ በሰሜን ኢትዮጵያ የሀገርን ህልውና ለማስጠበቅ እየተዋደቁ ለሚገኙ ጀግኖች አባላት ከዚህ በፊትም በደም ልገሳና በስንቅ ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።

በግንባር ለሚገኙ ሴት የሠራዊት አባላትና ሲቪል ሠራተኞች የሚሆን የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉንም ጠቅሰዋል።

የዕዙ አባላት ከደም ልገሳና ከቁሳቁስ ድጋፍ ባለፈ ወደግንባር በመሄድ የህይወት መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።