በኢትዮጵያ ስርዓተ -ምግብ ላይ ትኩረት ያደረገ ዓለም አቀፍ ጥናት ሊካሄድ ነው

148

አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 25/2013(ኢዜአ) በኢትዮጵያ ስርዓተ-ምግብ ላይ ትኩረት ያደረገ ዓለም አቀፍ ጥናት ሊካሄድ ነው።

ጥናቱ በካናዳ መንግስት ድጋፍ የሚካሄድ ሲሆን አንድ መቶ ሚሊዮን የካናዳ ዶላር በጀት ተይዞለታል።

በጥናቱ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ የኢትዮጵያ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት፣የካናዳው ዋግኒንገን ዩኒቨርሲቲ የሚሳተፉ ይሆናል።

ጥናቱም ከ2 እስከ 3 ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄደው ይህ ጥናት እናቶችና ህፃናት ላይ ትኩረት አድርጎ  በስርዓተ-ምግብ ላይ ያሉትን ክፍተቶች የሚገመግምና አዲስ ለወጣው ፖሊሲ ጭምር ግብዓት እንደሚሆን ተጠቅሷል።

በህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የምግብ ሳይንስና ስነ-ምግብ ምርምር ዳይሬክተር ዶክተር መርሻ ተሰማ እንዳሉት፤  ጥናቱ ከአመራረት እስከ መመገብ የሚደርሰውን የምግብ ዝግጅት ሂደት ሰንሰለት ይዳስሳል።

የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መኩሪያ ሃይሌ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ከምግብ አቅርቦትና ከህብረተሰቡ የመግዛት አቅም ማነስ ባሻገር ከግንዛቤ እጥረት የሚከሰት የተመጣጠነ ምግብ እጥረት መኖሩን ተናግረዋል።

የግንዛቤ እጥረቱን ለመፍታት የጤና ተቋማትን ጨምሮ ባለድርሻ አካላት በጥምረት መስራት እንደሚገባቸውና ይህም በጥናት መመለስ እንደሚቻል ጠቅሰዋል።

በመሆኑም ጥናቱ በሀገር ውስጥ ያሉ የጤናማ አመጋገብ ስርዓት ክፍተት ምክንያቶችና መፍትሄዎችን ይዞ ይመጣል ተብሎ ይጠበቃል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም