ኢንስቲትዩቱ በአዲሱ ዓመት የከፍታ መረጃ መሣሪያ ጥቅም ላይ ያውላል

180

አዲስ አበባ ነሃሴ 24/2013 (ኢዜአ) የጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት የመረጃ አቅርቦት ስራውን ለማሳደግ ከመጪው መስከረም ጀምሮ የላይደር ሴንሰር ወይም የከፍታ መረጃ መሣሪያ መጠቀም እንደሚጀምር አስታወቀ።

የላይደር ሴንሰር ቴክኖሎጂው ተቋሙ ከዚህ ቀደም የአየር ፎቶግራፍ ከሚያነሳባቸው ዘመናዊ ካሜራዎች የላቀ አገልግሎት እንደሚሰጥ የኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቱሉ በሻ ለኢዜአ ገልጸዋል።

ቴክኖሎጂው የኢትዮጵያን የአየር ፎቶግራፍ ሽፋን ያሳድጋል፤ የፎቶግራፍ መረጃን ተደራሽ ከማድረግ ባሻገርም የተለያዩ መረጃዎችን ማግኘት ያስችላል ብለዋል።

መሣሪያው የተደበቁ ነገሮችን የሚያሳይ በመሆኑ ለወታደራዊ ቅኝት እንዲሆን ለብሔራዊ ደህንነት በግብዓት ደረጃ እንደሚያገለግል ዋና ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል።

የኢኮኖሚና ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ተደራሽ ከማድረግ አንፃርም ከሕገ ወጥ ንግድና የመሬት ወረራ ጋር የተያያዙ እንቅስቃሴዎችን ለመቆጣጠር ያግዛል።

የገጠርና የከተማ ልማት፣ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች፣ የፊልምና ጥናታዊ ዘገባዎች ለመሥራት የላቀ አግልጋሎትም ይሰጣል።

የከፍታ መረጃ መሣሪያው አውሮፕላን ላይ ተገጥሞ መረጃ እንዴት እንደሚሰበሰብና መረጃው እንዴት ጥቅም ላይ እንደሚውል ለባለሙያዎች ሥልጠናም ተሰጥቷል።

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ የከፍታ መረጃ መሣሪያው ከመስከረም 2014 ዓ.ም ጀምሮ ሥራ ላይ ይውላል፤ የተለያዩ ተቋማትም የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ይሆናሉ።

ኢንስቲትዩቱ ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ጋር ውል የገባባቸው ፕሮጀክቶች በከፍታ መረጃ መሣሪያው አጋዥነት እንደሚከናወኑም ጠቁመዋል።

በቀጣይም ኢንስቲትዩቱ ማዕድን መለየት የሚያስችል ካሜራና ሰው አልባ አውሮፕላኖችን እንደሚገዛና ከሳተላይት ጋር የሚገናኙ ጣቢያዎች ለመክፈት ማቀዱን ዶክተር ቱሉ ገልጸዋል።

ይህም መረጃ ከማምረት ጎን ለጎን ችግር ፈቺና ፈጠራ የታከለባቸው የምርምር ሥራዎች ለማከናወን ከፍያለ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ነው የተናገሩት። 

የላይደር ሴንሰር ወይም የከፍታ መረጃ መሣሪያው በሰኔ 2013 ዓ.ም ሌይካ ቲሪያን ማፐር ቱ ከተሰኘ የስዊዘርላንድ ካምፓኒ ተገዝቶ ወደ አገር ውስጥ መግባቱ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ የአየር ፎቶዎች ሽፋን ከ2007 እስከ 2013 ዓ.ም ድረስ 43 በመቶ መድረሱን የጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም