በወላይታ ዞን የህብረተሰቡን እርካታ ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራ ተገለፀ

1191

ሶዶ ነሀሴ 6/2010 በወላይታ ዞን በአዲሱ የበጀት ዓመት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታት በሁሉም ዘርፍ የህብረተሰቡን እርካታ ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ገለጹ፡፡

የዞኑ ምክር ቤት ትናንት ባካሄደው 4ኛ ዙር 6ኛ ዓመት የስራ ዘመን 1ኛ መደበኛ ጉባኤ ዋና አስተዳዳሪን ጨምሮ አምስት የተጓደሉ የመምሪያ ኃላፊዎችን ሹመት አጽድቋል፡፡

ዋና አስተዳዳሪው ዶክተር ጌታሁን ጋረደው እደገለጹት የህዝብን አንድነት ማጠናከርና ለመልካም አስተዳደር ተጋላጭ የሚያደርጉ ጉዳዮችን በጥናት በመለየት የህብረተሰቡን እርካታ ለማረጋገጥ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

ለህዝቡ የመልካም አስተዳደር እጦት ምክንያት የሆኑ ተቋማትን ለመለየት ከሃይማኖት አባቶች፣ ሃገር ሽማግሌዎችና ከአከባቢ ተወላጅ ምሁራን ጋር በቅርበት እንደሚሰራም አስታውቀዋል፡፡

የህዝብረተሰቡን አንድነትና ህብረት በማጠናከር የመጠራጠርና ላለመግባባት መነሻ የሚሆኑ ችግሮችን የመለየት ስራም ትኩረት እንደሚሰጠው ገልፀዋል፡፡

የወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ፣ ብሄራዊ ማንነትን መገንባትና የተፈጥሮ እውቀቱን በተገቢው መንገድ በስራ ላይ እንዲያውል የሚያስችል ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ህዝቡንና ሃገሩን የሚወድ እንዲሁም ሙስናን የሚጸየፍ ወጣት ለመቅረጽ አሰራሮች እንደሚቀየሱም ተናግረዋል፡፡

የወጣቶችንና ህጻናትን ፍልሰትና ህገ ወጥ ዝውውር በተቀናጀ መልኩ ለማስቀረት የሚያስችል የምግብ ዋስትና ፕሮግራሞች ተግባራዊ እንደሚሆኑም ገልጸዋል፡፡

“በክልሉና አካባቢው በተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች ዙሪያ ጉዳት የደረሰባቸውን የማቋቋም ተግባርም ይከናወናል” ብለዋል፡፡ “ግብርናን ዘመናዊ በማድረግ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችል የግብይት አደረጃጀትን መቀየር ያስፈልጋል” ያሉት አስተዳዳሪው ይህን የሚያከናውን አገልጋይ መሪ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡

ህዝቡም ከጎናቸው በመሆን እንደሃገር የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ እንዲያጠናክር ጠይቀዋል፡፡

የዞኑ ምክር ቤት ዋና አፌ ጉባኤ አቶ ተዲላ ናደው በበኩላቸው ስልጣን ተጠያቂነት በመሆኑ ተሿሚዎች ጠንክረው መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

በሃገሪቱ የተፈጠረው የህዝብ መነቃቃት በተግባር እንዲደገፍ የትኩረት አቅጣጫዎችን በመለየት የተቀመጡ በጀቶችን በአግባብ ስራ ላይ ማዋልና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የዞኑ ምክር ቤትም አስፈፃሚ መስሪያ ቤቶችን ከመቆጣጠር ባሻገር ድጋፍ ለማድረግ ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡